በሚቀጥሉት አስር ቀናት አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ እንዲሁም መካከለኛ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
የምዕራብ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል።
በሌላ በኩል በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ደረጃ ያለው የዝናብ መጠን እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብሏል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብ እንዲሁም በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ርጥበት ይኖራቸዋል ብሏል።
ይህም በአመዛኙ ለግብርና ስራ እንቅስቃሴ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጠቁሟል።
በአብዛኞቹ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገጸ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚጠበቅ ትንበያዎች እንደሚያሳዩ ተመላክቷል።
የአባይ፣ የባሮ አኮቦና የኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ርጥበት የገጸ ምድር ውሃ እንደሚያገኙም አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ የታችኛው ኦሞ ጊቤና የአዋሽ ተፋሰስ ከቀላል እስከ መካከለኛ ርጥበት እንዲሁም የዋቤ ሸበሌ ተፋሰስ ቀላል መጠን ያለው የገጸ ምድር ውሃ እንደሚኖራቸው ጠቅሷል።