አንድ የ13 ዓመት አፍጋናዊ በአፍጋኒስታኑ ካም ኤር የመንገደኞች አውሮፕላን የጎማ ክፍል ውስጥ ተደብቆ ከአፍጋኒስታኗ ዋና ከተማ ካቡል ተነስቶ ከህንዷ ዴልሂ ያለ ጉዳት መድረሱ የዜና አውታሮች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
በሰሜን አፍጋኒስታን ኩንዱዝ ከተማ ነዋሪ የነበረው ታዳጊው አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ በዴልሂ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወዲያና ወዲህ ሲል መገኘቱን የህንድ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
የአየር ማረፊያው የደህንነት አካላት ታዳጊውን ወደ ሃገሩ ከመመለሳቸው በፊት ለሰዓታት ምርምራ አድርገውበታል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
ታዳጊው በሃገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመሸሽ መሄድ ያሰበው ወደ ኢራን ቢሆንም አውሮፕላኑ ወደ ዴልሂ እንጂ ወደ ቴህራን አለመሄዱን ሳያውቅ ተደብቆ ሊጓዝ መቻሉን ተናግሯል፡፡
ከዚህ ቀደም በርካቶች በዚህ መንገድ አደገኛ ጉዞን ያደረጉ ቢሆንም ጥቂቶች ግን በህይወት መገኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የዚህ ታዳጊ ከአደገኛ ጉዞ በህይወት መትረፍ በርካቶችን ያስገረመ ሆኗል፡፡
በሊያት ካሳሁን