እጅ ለእጅ ተያይዘን ለትውልድ የፀናች ሀገር እንገንባ ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ጠየቁ

You are currently viewing እጅ ለእጅ ተያይዘን ለትውልድ የፀናች ሀገር እንገንባ ሲሉ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ጠየቁ

AMN – መስከረም 13/2018 ዓ.ም

እጅ ለእጅ ተያይዘን ለትውልድ የፀናች ሀገር እንገንባ ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የጋራ ኮሚቴ የኮሚሽኑን የመጀመሪያ ሩብ አመት የስራ እንቅስቃሴ እና ቀጣይ የትኩረት ጉዳዮችን የተመለከተበት የውይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ኮሚሽኑ ባለፉት አመታት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምክክሩ ሂደቱ እዚህ እንዲደርስ ጉልህ አስተዋፅ እያበረከቱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ድርጅቶቹ ከኮሚሽኑ ጋር በመተባበር እየሰሩት ያለውን ስራ ያደነቁት ኮሚሽር መላኩ፣ “እጅ ለእጅ ተያይዘን ለትውልድ የፀናች ሀገር እንገንባ” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ተረፈ ደጊቲ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሰራ ላለው ስራ አመስግነዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከቀበሌ እስከ ዳያስፖራ ድረስ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በማካተት ምክክር እያካሄደ መሆኑን በተግባር አይተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት እናደንቃለን ማለታቸውን ከኮሚሽነ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ምክር ቤቱ በቀጣይ ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል፡፡ በመድረኩ ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ወራት ያከናወናቸው አበይት ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያ በቀረበው የአፈፃፀም ገለፃ፣ ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ወራት በትግራይ ክልል ምክክር ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎችን ስለማከናወኑ፣ በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ እያሰባሰበ ስለመሆኑ እንዲሁም ዋናውን ሀገራዊ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያግዙ ስራዎች መጀመራቸው ተመላክቷል፡፡

በትግራይ ክልል ምክክር ማካሄድ፣ የዳያስፖራ ምክክር መድረኮችን ማጠናቀቅ እንዲሁም ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ማካሄድና አፈፃፀሙን መከታተል የኮሚሽኑ የቀጣይ ትኩረቶች መሆናቸውም ተገልጧል፡፡ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደከዚህ ቀደሙ በቀጣይ የኮሚሽኑ ስራዎች ላይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ተጠይቋል፡፡

የምክክሩን ሂደት ለመደገፍ በርካታ ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱን የገለፀው ምክር ቤቱ ከመስከረም 22-ታህሳስ 30 የሚቆይ በምክክሩ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሳምንታዊ የራድዮ ፕሮግራም ለማዘጋጀትና ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የኮሚሽኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች በስፋት ለህዝብ ተደራሽ የሚሆኑበትና በቅርቡ የሚጀመር የዲጂታል ሚድያ ንቅናቄ መርሃግብር ማዘጋጀቱንም በዚሁ መድረክ አመላክቷል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review