የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ጋር በሀገራዊ የፀጥታ ዕቅድ ላይ በዋና መሥሪያ ቤቱ ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ላይ በሰጡት የሥራ መመሪያ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን በርካታ ፀረ-ሰላም ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀው በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት እንዳይሰፍን የሚንቀሳቀሱ አሸባሪና ፅንፈኛ ቡድኖችን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የፀጥታና ደኅንነት ተቋማቱ በተጠናከረ ዝግጅትና ቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል አያይዘውም በቀጣይ ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተው ከፊታችን የሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወኑ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት በሀገራችን የሚኖሩ ሕዝባዊ፣ መንግስታዊ እና ሀይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ በተዘጋጀው የፀጥታ ዕቅድ ላይ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ፣ የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ ኦፕሬሽን ለማካሄድ የሚያስችል ኦረንቴሽንና ስምሪት በመውሰድ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች በቅንጅት እንደሚሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡