የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ/ም የሚከበረው የደመራና መስከረም 17 ቀን 2018 ዓ/ም የሚከበረው የመስቀል በዓልን አስመልክቶ ከኃይማኖት አባቶችና ከበዓሉ አከባበር ኮሜቴ ጋር በፀጥታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የተውጣጣ የደመራና የመስቀል በዓላት ዝግጅት ኮሚቴ በፀጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ አጠቃላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
በቀረበው ሪፖርት በየእርከኑ ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር ቅንጅት ተፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን በየደረጃው ለሚገኙ የኃይማኖት አባቶችና በዓሉን ለሚያስተባብሩ ወጣቶች በዓሉ ኃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ውይይት መደረጉና ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር በመነጋገር ለበዓሉ ታዳሚዎች የሚያገለግል የይለፍ ካርድ በጥንቃቄ መዘጋጀቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ላይ የጠቅላይ መምሪያው አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንደተናገሩት ከኃይማኖት አባቶችና ከበአሉ አከባበር አስተባባሪዎች እና ኮሚቴዎች ጋር ውይይት መደረጉ በጋራ ለመስራት እና ትስስሩን ለማጠናከር ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የኃይማኖት አባቶች፣ የበዓሉ አከባበር ኮሚቴዎች እና የእምነቱ ተከታዮች እንደ ከዚህ ቀደሙ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ያላቸውን ትስስር አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው በዓሉ በሠላም እንዲከበር በልዩ ልዩ መድረኮች የበዓሉ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት፣ ከህብረተሰቡ፣ ከልዩ ልዩ አደረጃጀቶችና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን አስታሰው የበዓሉ አከባበር ኮሚቴዎች እና አስተባባሪዎች ከፀጥታ አካላቱ ጋር በትብብር መንፈስ በመስራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የኃይማኖት አባቶች ቤተክርስቲያኒቷ በዓሉ በድምቀት እና በሠላም እንዲከበር ድርብ ኃላፊነት እንዳለባት ገልፀው ይህንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲቻል ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጸጥታ አካላት አመራሮች በዓሉ በሠላም እንዲከበር እያደረጉት ስላለው ድጋፍና ትብብር ምስጋናቸውን ማቅረባቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።