በሚቀጥሉት 4 አመታት በአለም አቀፍ ደረጃ 3 ትሪሊየን ዶላር ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ግንባታ ወጪ እንደሚደረግ ተገለጸ

You are currently viewing በሚቀጥሉት 4 አመታት በአለም አቀፍ ደረጃ 3 ትሪሊየን ዶላር ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ግንባታ ወጪ እንደሚደረግ ተገለጸ

AMN – መስከረም 14/2018 ዓ.ም

አለም በሰው ስራሽ አስተውሎት ግንባታ የሚያደርገውን ፉክክር ባጠናከረበት በዚህ ጊዜ ዘርፉ በትሪሊየን ዶላሮች የሚገመት ገንዘብ ፈሰስ እየተደረገበት ይገኛል።

በፈረንጆቹ እስከ 2029 ድረስ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ ማዕከል ግንባታ 3 ትሪሊየን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ቢቢሲ አስነብቧል። ይህን ገንዘብ በንጽጽር ለማስቀመጥ ከአጠቃላይ የፈረንሳይ ኢኮኖሚ ጋር የሚስተካካል እንደሆነም ዘገባው አክሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አገልግሎቶችን እና ፈጠራዎችን አቅም ለማፋጠን በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት 100 የመረጃ ማዕከላት ይገነባሉ። ከነዚህ መካከል የተወሰኑት 30 ቢሊዮን ዶላር የሚወጣባቸው ማዕከላት በዚህ ወር በማይክሮሶፍት የሚገነቡ ይሆናል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ ማዕከላት (AI data centres) ከ ”ኮምፒውተር ዳታ ሰርቨር” ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆን ነገር ግን በሚጠቀሙት ሀይል እና በሚቀበሉት የመረጃ ብዛት የተለዩ ናቸው። ከዚህ ባለፈም ሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን ቋንቋ የሚያሰለጥኑ እና ለሚጠየቁት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ የሚያስችሉ ሶፍትዌሮች እና ቺፕሶች የዚህ የመረጃ ማዕከል ግንባታ አካል ናቸው።

ማይክሮሶፍት፣ ጎግል እና አማዞን ዌብ ሰርቪስ በማዕከላቱ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ፉክክር እያደረጉ ይገኛሉ። ማዕከላቱን ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ ሀይል የሚጠይቅ መሆኑን ተከትሎ ሀገራት ከማዕከላቱ ግንባታ ባለፈ ይህን የሚያንቀሳቅስ የሀይል አቅርቦትን ማሟላት ላይ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።

የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ከሜጋዋት በ1000 እጥፍ የሚበልጥ በጊጋዋት ደረጃ የሚገመት ሀይል እንደሚያስፈልግ እና በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለመቀነስ ራሱን የቻለ የሀይል አማራጭ እንዲገነባ በመጠየቅ ላይ ነው።

በአሁኑ ወቀት አሜሪካ በመንግስት እና በግል ደረጃ ከ471 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ በአለም ቀዳሚ ስትሆን ቻይና እና ዩናይትድ ኪንግደም በ100 ቢሊየን ዶላሮች እየተከተሉ ይገኛሉ።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review