ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችን በተለይም ግብ ሰባትን በማሳካት ንጹህ የኃይል አቅርቦትን ከማሳደግ አንጻር የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው አስገነዘቡ።
ፕሬዚዳንት ታዬ ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት አናሌና ቤርቦክ ጋር ተወያይተዋል። በዚሁ ወቅትም፤ በወቅታዊ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ላይ መክረዋል።
እንዲሁም በኢትዮጵያ ልማት፣ ቀጣናዊ ሰላም እና ደኀንነትን ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ የትኩረት መስኮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል። የባለብዙ ወገን ግንኙነት እና የጋራ ደኀንነት መርሆዎችን ለማስጠበቅ የጋራ ጥረቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንት ታዬ አስገንዝበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችን በተለይም ግብ ሰባትን ለማሳካት ንጹህ የኃይል አቅርቦትን በማሳደግ ረገድ ያለውን ፋይዳም አስረድተዋል። መሰል ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮችን የበለጠ ለማጠናከር መልካም ዕድል ይዘው እንደሚመጡ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ቤርቦክ በበኩላቸው፤ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መርሆችን ማክበር እና መጠበቅ ለዓለም ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።