ስምንት ክለቦች የሚሳተፉበት የአዲስ አበባ ከተማ “ህዳሴ ዋንጫ” ውድድር የፊታችን ዕሁድ ይጀምራል

You are currently viewing ስምንት ክለቦች የሚሳተፉበት የአዲስ አበባ ከተማ “ህዳሴ ዋንጫ” ውድድር የፊታችን ዕሁድ ይጀምራል

AMN – መስከረም 14/2018 ዓ.ም

19ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) “ህዳሴ ዋንጫ” በሚል ስያሜ ከእሁድ ጀምሮ እንደሚከናወን ተገለፀ።

የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር በስምንት ክለቦች መካከል እንደሚከናወን ዛሬ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነግሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ መቻል ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

ዛሬ በተከናወነው የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት በምድብ “ሀ” ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ አዳማ ከተማ እና መቻል ፤

በምድብ “ለ” ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮ. ኤሌክትሪክ ፣ ሸገር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተደልድለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ “ህዳሴ ዋንጫ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ውድድር የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ስታዲየም መከናወን ይጀምራል።

ተመልካቾች ወደ ስታዲየም ገብተው እንዲታደሙ እየተሰራ እንደሆነም በመግለጫው ተነስቷል።

በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ፤ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዲመለሱ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ብዙ ነገር ያሳጣናል ያሉት ሃላፊው ይህን የሚታገስ አካል ስለሌለ ሁሉም ይህን አውቆ እንዲሰራ አሳስበዋል።

አቶ ዳዊት በተለይ ክለቦች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ከደጋፊዎቻቸው ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review