ከሰሜን ፊሊፒንስ በተነሳውና በታይዋን በተከሰተው “ታይፉን ራጋሳ” በተሰኘው የዓመቱ ከባድ አውሎ ነፋስ፣ የ14 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ 124 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተገልጿል፡፡
ከሰሜን ፊሊፒንስ የተነሳው ከባድ አውሎ ነፋስ በታይዋን ጉዳት አድርሶ በማለፍ የቻይና ከተሞችንም መምታቱ ተነግሯል፡፡
ይህንን ተከትሎም ቻይና ከጉዋንደንግ ግዛት ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማድረጓን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ምንም እንኳን እስከ አሁን አውሎ ነፋሱ ቀጥታ ሆንግ ኮንግን ባይመታም፣ በከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ ጠንካራ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በማስከተል 62 ሰዎችን ለጉዳት መዳረጉም ተመላክቷል፡፡
በዚህም ከ400 በላይ የዛፎች መውደቅ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት መከሰቱ ተዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ ህንድ በ39 ዓመታት አይታው የማታውቀውን ከባድ ዝናብ ማስተናገዷ ተገልጿል፡፡
በምስራቅ ህንድ በምትገኘው ኮልካታ ከተማ በዘነበ ከባድ ዝናብ፣ የ10 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ ዘጠኙ ከኤሌክትሪክ ጋር ንክኪ በነበረው ውሃ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡
በከተማዋ የመኖሪያ እና ንግድ ስፍራዎችን ጨምሮ ቁልፍ መንገዶች በጎርፍ መጥለቅለቃቸውንና የባቡር አገልግሎትም መስተጓጎሉን ዘገባው አያይዞ ገልጿል፡፡
በሊያት ካሳሁን