በዓላቱ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ

You are currently viewing በዓላቱ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ

AMN – መስከረም 14/2018 ዓ.ም

የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የመስቀልና ኢሬቻ በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር የማጠቃለያ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

በዘንድሮ ዓመት በእምርታና በማሰራራት ታጅበው የሚከበሩት የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሙሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ ከበደ ተናግረዋል።

በዓሉን የምናከብረው ትልቅ ታሪክ በሰራንበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በዚህም መዲናዋ እንደተለመደው አስተማማኝ ሰላሟን ታስቀጥላለች ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓልን ስናከብር በተለይ የደመራ ቦታዎች ከከፍተኛ የሃይል ተሸካሚ የኤሌክትሪክ መስመሮች መራቅ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።

በዓላቱ የፍቅርና የአብሮነት መገላጫ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሚደቅሳ፤ በዓላቱ ሀይማኖታዊ ትውፊቱን ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲከበሩ የማድረግ የፀጥታ አካላቱ ኃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል።

በበዓላቱ ወቅት እኩይ ተግባር የሚፈጽሙ ፀረ-ሰላሞችን በመከታተል ለህግ ማቅረብ እንደሚገባም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተነግረዋል፡፡

በተጨማሪም በበዓላቱ ላይ ፀብ አጫሪ የሆኑ መልእክቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ሎጎዎችና ሌሎችም መልእክቶችን ማስተላለፍ የሚገባ ባለመሆኑ የፀጥታ መዋቅሩ በትኩረት መስራት እንደሚገባውም ተናግረዋል።

መዲናዋ የተለያዩ የአለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማ ከመሆኗ አንጻር የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጀች ያለች ከተማ በመሆኗ፤ በዓላትን አስታከው የሚመጡ የድምፅ ብክለቶች እንዳይፈጠሩ ርችት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመስቀል ደመራን በዓል ስናከብር የሀይማኖት አባቶች ባስቀመጡት ስርአት እንዲሁም ኢሬቻ ሲከበር ደግሞ አባ ገዳዎች ባስቀመጡት ስርአት መሰረት ብቻ መከበር እንደሚገባውም አቶ ሚደቅሳ ከበደ ተናግረዋል።

ከፀጥታ አካላቱ በተጨማሪም ከሀይማኖት አባቶች፣ ከአባ ገዳዎች እንዲሁም ከወጣቶች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review