ለ2ኛ ጊዜ የሚከናወነው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚከናወን ተገለፀ።
ዛሬ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ፅ/ቤት ውድድሩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈፃሚ አባላት ተገኝተዋል።
የወጣቶችን ተሳታፊነት ማሳደግ ፣ ብቁ አትሌቶችን ማፍራት እና የሀገር ገፅታ መገንባት የውድድሩ ዋና ዋና አላማዎች እንደሆኑ በመግለጫው ተነስቷል።
ውድድሩ በአንጎላ ለሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ እንዲሁም በሴኔጋል ለሚከናወነው የዓለም የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ እንደሚረዳም ተጠቅሷል።
ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በሚሳተፉበት የዘንድሮው ውድድር ላይ 20 ስፖርቶች ለፉክክር ቀርበዋል።
በውድድሩ መሳተፍ የሚችሉት እድሜያቸው ከ14 እስከ 17 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎች ብቻ እንደሆኑ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ገልፀዋል።
በእድሜ ጉዳይ ጠንካራ ስራ ለመስራት እንደተዘጋጁም ተነግረዋል።
የህክምና ባለሞያዎች ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር አብረው እንደሚሰሩ እና ለስፖርተኞቹ የኤም አር አይ(MRI) ምርመራ እንደሚደረግ ፕሬዝዳንቱ በመግለጫቸው አንስተዋል።
የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ከአራት ዓመት በፊት በሃዋሳ ያከናወነው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 2ኛውን ውድድር በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቅምት 8 እስከ 15 የሚያከናውን ይሆናል።
በሸዋንግዛው ግርማ