የሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ በክልላችን አስተባባሪዎችና አመራሮች ቸልተኝነት ደስታችንን ባለመግለፃችን አዝነናል ሲሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት የትግራይ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል መለስ በበኩላቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በኩል የተሰጠው የደስታ መግለጫ በቂ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለስኬት እንዲበቃ ኢትዮጵያዊያን በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው ጭምር የላቀ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ከ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላ ሲጠናቀቅም በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ህዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣት ደስታውን ገልጿል።

በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ህዝቡ ደስታውን ወጥቶ ሲገልፅ እንደ ሌሎች ሁሉ ለግድቡ ስኬት አስተዋፅኦ የነበረው የትግራይ ህዝብ ደስታውን ወጥቶ እንዳይገልፅ ለምን ተነፈገው?
የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች አቶ ገብረ ስላሴ ኃለፎም እና አቶ አለማየሁ አብርሃ፤ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰታቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሁሉም ክልሎችና ከተሞች ዜጎች ደስታቸውን የገለጹ ቢሆንም በትግራይ ክልል ግን በአመራሮችና አስተባባሪዎች ቸልተኝነት ደስታችንን መግለጽ ባለመቻላችን አዝነናል ብለዋል።
አቶ ገብረ ስላሴ ”የትግራይ ህዝብ የመንግስት ሰራተኛ አርሶ አደር ቦንድ በመግዛት ግንባታው እስኪጠናቀቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ እንደ ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በትግራይም ህዝቡ ወጥቶ ደስታውን መግለጽ ነበረበት” ብለዋል።

”የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ በመብቃቱ ወጥተን ደስታችንን ልንገልጽ ይገባ ነበር። ሲመረቅ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማን” ያሉት ደግሞ አቶ አለማየሁ ናቸው።
ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች አቶ ኃይለስላሴ በየነ፣ ኤፍሬም መውጫ እና ክንደያ በርሄ፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሁሉም ጥረትና ትብብር ለስኬት በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ በትብብርና ጽናት በጋራ መስራት ከተቻለ የማይቻል ነገር የማይፈፀም ፕሮጀክት እንደሌለ በተግባር ያሳየንበት ነው ብለዋል።

በመሆኑም በህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳየነውን ትብብር በማጠናከር ሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት መዘጋጀት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ምላሽ ለማግኘት ኢዜአ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት የትግራይ ማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ ሚካኤል መለስ በጉዳዩ ዙሪያ ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥረት አድርጓል።
ኃላፊውም ”የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን ተከትሎ የትግራይ ህዝብ የደስታ መግለጫ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት በኩል በመሰጠቱ ከዚህ በላይ የምገልፀው ነገር የለኝም” ሲሉ በስልክ ገልጸዋል።