ህዝባዊ በዓላት የሃገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑን ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ገለፁ

You are currently viewing ህዝባዊ በዓላት የሃገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑን ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ገለፁ

AMN – መስከረም 15/2018 ዓ.ም

እንደ መስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት ያሉ ህዝባዊ በዓላት ከውጪ ጎብኚዎች በተጨማሪ የሃገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ፋይዳቸው ከፍተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

መዲናዋ ሁሌም ለበዓላት ዝግጁ መሆኗን የተናገሩት ሃላፊዋ፣ በዓላት በተዋበች እና ደረጃዋን በጠበቀች ከተማ ላይ ሲከበሩ የተለየ ከፍታ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

የቱሪስት መስህብ ለሆኑት መጪዎቹ የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት የከተማዋ ዝግጁነት ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሃላፊዋ፤ ይህ ሁኔታ በአለም ላይ ትልቅ ተፅእኖ የምንፈጥርበት እና የቱሪስት ፍሰትን የሚጨምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከማህራዊ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላላቸው በዓላቱ ከማክበሪያ ቦታ ጀምሮ ከበፊቱ በተለየ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ገልፀዋል፡፡

የማንነት መገለጫዎቻችን፣ ህዝባችን የትብብር እና የመልካም እሴት መገለጫዎቻችን የሆኑት የመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት፤ ከዛም ባለፈ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እድል የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

በዓላቱ ከውጪ ጎብኚዎች በተጨማሪ የሃገር ውስጥ ጎብኚዎችን ከማሳተፍ አንፃር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የተናገሩት ሃላፊዋ፤ በዚህም የሃገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

የአንድ ሃገር ቱሪዝም ዘላቂነት የሚኖረው ሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ሲጨምር ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ ይህንን በመገንዘብ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም የሃገሬው ሰው የጉብኝት ባህሉን እንዲያሳድግ ማድረግ በሚል እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የሃገር መቆሚያዋ ባህል ነው ያሉት ሃላፊዋ፤ ህዝባዊ በዓላትም የጉብኝት ባህልን ማሳደግና ባህል ማድረግ እንደሚችሉም ገልፀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምርት እና አገልግሎትን ማስተዋወቅም ከውጭ ጎብኚዎች የሚገኘውን ገቢ የማሳደግ እቅም ያለው በመሆኑ በዚህ ረገድም መስራት እንደሚያስፈልግ ሃላፊዋ አንስተዋል፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review