የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በነገው ዕለት ተከብሮ ይውላል፡፡ ይህንኑ በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቤተ እምነቶች የሃይማኖት አባቶች፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፤ ወጣቶችና የልዩ ልዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች የተሳተፉበት የመስቀል አደባባይ የደመራ ቦታ የማጽዳት ዘመቻ ተካሄዷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእቅድና ልማት መምሪያ ኃላፊ መላከ ሕይወት አባ ወልደየስ ሰይፉ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የአብሮነት መገለጫ የሆነው የመስቀል በዓል ማክበሪያ ቦታ ለማጽዳት የተገኙትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

መስቀል፣ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ያለውን የመጨረሻ ፍቅሩን የገለጸበት መሆኑን ጠቅሰው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደመራ ቦታን በማልማት ያከናወነው ተግባር ቦታውን ከማሳመር ባለፈ በአዕምሯችን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ ማጽዳት እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ወክለው ንግግር ያደረጉት ሃጂ አወል ሃምዛ በበኩላቸው፣ በዩኔስኮ የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል የኢትዮጵያውያን የጋራ ጌጥና ውበት በመሆኑ አክብረን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን ብለዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ፣ የመስቀል በዓል ለዘመናት በኢትዮጵያ ሲከበር የኖረ ቢሆንም ዘንድሮው ግን አባይን ገድበን ለሕዝባችን ባበረከትንበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል የአዲስ አበባ ከተማን መልካም ገጽታ ለተቀረው ዓለም የምሳይበት ነው ሲሉም ነው ኢንጂነር ወንድሙ የገለጹት፡፡
የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ በመስቀል ደመራ ቦታው ማጽዳት ላይ በጋራ መቆማችን ብዙ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ኢትዮጵያዊ የወንድማማችነትና አብሮ የመኖር እሴታችን አጠናክረን ለትውልድ ልናወርሰው ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በምትኩ ተሾም