አውስትራሊያ ታዳጊዎች ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንን እንዳይጠቀሙ የወሰደችው የክልከላ እርምጃ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አድናቆትን አግኝቷል።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታ ድርጅት (ተመድ) ስብሰባ ላይ፣ ማህበራዊ ሚዲያ በህጻናት ላይ የሚያስከትላቸው ችግሮች በየጊዜው እየተባባሱ መምጣታቸውን አስገንዝበዋል።
በዚህም ሀገራቸው ታዳጊዎች ማህበራዊ ሚዲያን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ህግ ማስቀመጧን ያስታወቁ ሲሆን፣ ትግበራውም በፈረንጆቹ ታህሳስ ወር እንደሚጀምር መግለፃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
መንግስታት እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ በመከልከል የመጀመሪያዋ ሀገር የሆነችውን አውስትራሊያን በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውም ተመላክቷል።
አውስትራሊያ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች፣ የተጠቃሚዎችን ዕድሜ ለመገምገም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና የባህሪ መረጃዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉም እየጠየቀች ነው።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮንደርሌይንን ጨምሮ በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ የታደሙ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች የአውስትራሊያን እርምጃ አድንቀዋል፡፡
በታምራት ቢሻው