በአዲስ አበባ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባህል እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

You are currently viewing በአዲስ አበባ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባህል እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ

AMN – መስከረም 15/2018 ዓ/ም

በአዲስ አበባ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባህል እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

በባለፉት አመታት በከተማው ለከፋ ችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል በከተማ አስተዳደሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ የመዲናዋ የልማት ሥራ ለራስ ከመጠቀም ባሻገር ለሌሎች በመትረፍ ማህበራዊ ሃላፊነቷን እየተወጣች ያለች ከተማ ነች ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በዚህም በከተማዋ በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራት ስራዎች መከናወናቸውን ከነዚህም መሀከል፤ ምቹ ባልሆነ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ፣ ለከፋ ችግር የተጋለጡ እና አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ዋንኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ 1 ሺህ 671 ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን አስረድተዋል ፡፡

በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ከ1ዐ አመት በፊት ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ እግራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው አቶ አለሙ ኢቲቻ ፀሐይና ዝናብን በየተራ ከምታስተናግደው ጐጆቸው ከ36 ዓመት በላይ ኖረዋል፡፡

የቤታቸው ስፋት 2 ሜትር በ2 ሜትር እንደነበረች የሚገልፁት አቶ አለሙ፤ ከአካል ጉዳተኝነታቸው ጋር ተዳምሮ ጥበቱ እንደልብ መንቀሳቀስ ይከለክላቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተደደሩ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት አማካኝነት ምቹ የሆነ የመኖሪያ ቤት ገንብቶ በመረከባቸው ከአስቸጋሪ ህይወት መላቀቃቸውን ለኤ.ኤም. ኤን የተናግረዋል ፡፡

“እንዲህ ያለ ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት አገኛለሁ ብየ እንኳን በእውኔ በህለሜም አስቤው አላውቅም“ የሚሉት አቶ አለሙ በዚህም እጅግ ደሰተኛ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡

ሌላዋ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ወ/ሮ ዝናሽ ቸኮል ከ32 ዓመት በላይ ፀሐይ፣ ዝናብ፣ ብርድና ንፋስ በቤቴ ውስጥ አብረዋቸው ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው ፤ በዚህም ሳቢያ ለከፋ የጤና እና የሥነ ልቦና ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ በክረምት የበጐ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር፤ ምቹ የመኖሪያ ቤት ተሰርቶ በመረከባቸውን ገልፀው “ከእንግዲህ የምጦርበትን ቤት በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ የማህበረሰብ ተሳትፎና የበጐ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው 2 ሺህ 5ዐዐ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ፤ በበጐ ፈቃድ አድራጊ ባለሀብቶች ተሳትፎ የ3 ሺህ 154 ቤቶች ግንባታ ተጀምሯል፡፡

እስካሁን 1 ሺህ 671 ቤቶችን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍም መቻሉን ፣ በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወነ የሚገኘው የክረምት በጐ ፈቃድ አገልግሎት እስከ መስከረም 3ዐ የሚቀጥል መሆኑ እና ይህም

የሚሰራው ባለሀብቱን በማስተባበር ጭምር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ይህ ተግባር ደግሞ በከተማዋ የበጎ አድራጎት ስራ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠናከረ እና ባህል እየሆነ መምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በ-በረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review