በዓላትን በአብሮነት ማክበር ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን እንደሚያጎለብት የሀይማኖት አባቶች ገለጹ

You are currently viewing በዓላትን በአብሮነት ማክበር ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን እንደሚያጎለብት የሀይማኖት አባቶች ገለጹ

AMN መስከረም 15/2018

በዓላትን በአብሮነት ማክበር ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን የሚያጎለብት በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል ሲሉ በጅማ ከተማ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ።

በጅማ ከተማ የተለያዩ እምነት ተቋማት የሀይማኖት አባቶች የመስቀል ደመራ የሚከበርበት ስፍራን በጋራ አጽድተዋል።

በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጅማ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ሰላም ተስፋሚካኤል አሰፋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓሉን ለማድመቅ የተለያዩ ሀይማኖቶች አባቶች ያሳዩት መተባበር የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በጅማ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ሀይማኖቶች አባቶች ጋር በመከባበርና በወንድማማችነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳለቸው አንስተው፤ የከተማ አስተዳደሩና የጸጥታ አካላትም በየዓመቱ ለበዓሉ መከበር አብሮነታቸው አልተለየንም ብለዋል።

የአደባባይ በዓላት በተሳካ መልኩ እንዲከበሩ አብሮነትን ማጎልበት ይገባናል ብለዋል። የጅማ ከተማ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሐፊ ሀጂ ቢያ አባመጫ በበኩላቸው፤ ጅማ ከተማ የሀይማኖቶች መከባበርና መደጋገፍ የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬም በከተማው የሚገኙ የእምነት ተቋማት የሀይማኖት አባቶች የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በማጽዳት አብሮነታቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

ህብረትና አንድነት ለሀገር ሰላም ግንባታና ልማት ትልቅ ጥቅም አለው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የጅማ መካነ እየሱስ ባልደረባ ቄስ ደበላ ቢቂላ ናቸው።

አብሮነታችንን በማስቀጠል ለሀገራችን አንድነትና ሰላም እየጸለይን፤ አንድነታችንን የበለጠ እናጠናክራለን ሲሉ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጣሀ ቀመር፤ በከተማችን የሚከበረውን የደመራ በዓል በአብሮነት እንዲከበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አከናውነናል ብለዋል።

በተለይም በከተማው የሚገኙ የተለያዩ የሀይማኖት አባቶች ያሳዩት መተባበርና አብሮነት የሚበረታታ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው ያሉት።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review