የመስቀል ደመራ በዓል በአገራችን በአደባባይ ከሚከበሩ ታላላቅ በዓላት መካከል አንዱ ነዉ።
በዓሉ በዋናነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሲቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ከተቀበረበት ቦታ በንግስት እሌኒ አማካኝነት ተቆፍሮ መገኘቱን በማስመልከት የሚከበር በዓል እንደሆነ የሀይማኖት ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ባማረና በደመቀ መልኩ ይከበራል፡፡ በዓሉ በታላቅ ድምቀት ከሚከበርባቸው የሃገራችን አካባቢዎች መካከል ዓዲግራትና አካባቢው ተጠቃሽ ነው፡፡
በዓሉ በዓዲግራት ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን፣ በተለይ በ2009 ዓ.ም በከተማዋ ተራራማ ቦታ ላይ የተተከለው 21 ሜትር ቁመት የሚረዝመው መስቀል፣ ለከተማዋ ውበት ከመሆን አልፎ ለበዓሉም ድምቀትን ያላብሳል፡፡
የከተማው ነዋሪዎች በመስቀል ደመራ ዕለት በተለያዩ አቅጣጫዎች ችቦ ለኩሰው ወደ ደመራው ቦታ በማምራት ዋናው ደመራ እስኪለኮስ ድረስ በደመራው ዙሪያ እየተጫወቱ ይቆያሉ፡፡
በበዓሉ መዳረሻ ሳምንታት አካባቢ እናቶች በአካባቢው ተወዳጅ የሆነውን ባህላዊ ምግብ ጥሕሎና ሌሎች ባህላዊ የምግቦች ከጠጅ ጋር ያዘጋጃሉ፡፡
በተመሳሳይ አባወራ ወንዶች ደግሞ ለእርድ የሚሆኑ በሬዎችን እና በጎችን፤ እንዲሁም ለልጆች አልባሳትን ከመግዛት ባለፈ፣ በቤት ውስጥ የሚያስፈልጉ ነገሮችን የማሟላት ሃላፊነት ይወጣሉ፡፡
ሌላኛው የመስቀል ደመራ በዓልን በዓዲግራትና በአካባቢው ሲከበር ለየት የሚያደርገው ነገር፣ በበዓሉ ሳምንት ከብቶች የሚመገቡት ሳር ሁሉ በጋራ ይሆናል፡፡
የበዓሉን መዳረስ ተከትሎ እስከ በዓሉ ማግስት ድረስ ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች የተለያዩ ዜማዎችን በማዜም ይጫወታሉ፤ ይጨፍራሉ ፡፡
በዓዲግራትና በአካባቢው የሚከበረውን የመስቀል ደመራ በዓልን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እና በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የአከባቢው ተወላጆች ወደ ስፍራው በመምጣት ይታደማሉ፡፡
የዓዲግራትና አካባቢው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ከሀይማኖታዊ ትውፊቱ ባለፈ፣ ታላቅ የቱሪስት መስህብም እየሆነ መምጣቱን ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገቡ የአገራችን ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።
በአስማረ መኮንን