ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሩሲያ እየተካሄደ በሚገኘው በዓለም የአቶሚክ ሳምንት ጉባኤ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሐ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች ብለዋል። ኢትዮጵያ የሚሰሩ እና አቅም ያላቸው ወጣቶች አሏት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተሞች እየዘመኑ እና ኢንዱስትሪዎች እያደጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ትገኛለች ብለዋል፡፡በኢትዮጵያ በርካታ የልማት እቅዶች እንዳሏት በመግለጽ እቅዶቹ አስተማማኝ፣ ንፁህ እና ቀጣይነት ያለው የሃይል አቅርቦትን የሚጠይቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የውሃ፡ የፀሐይ እና የንፋስ ኃይል ብቻ እየተጠቀመች ለወደፊት ያሰብነውን ያህል ማደግ አንችልም ብለዋል። ኢትዮጵያ ከአስር አመታት በላይ በአረንጓዴ ልማት መሪ ሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቁርጠኛነታችን ምልክት መሆኑን ያሳየንበት ነው ብለዋል፡፡

ራዕያችን ከዚህ ያለፈ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኒውክለር ቴክኖሎጂ አስተማማኝ ሃይል ለመፍጠር እና ለጠንካራ ደህንነት እንዲሁም የውሃ አጠቃቀምን ምቹ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ኒውክለር የሃይል ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተማሪዎች እውቀት ለገበሬዎች ምርታማነት እንዲሁም ለህመምተኞች ፈውስን ይሰጣልም ብለዋል፡፡
የኒውክለር ሃይልን በጥንቃቄ በማቀድና ጥቅም ላይ በማዋል ጠንካራ የሀገር ውስጥ አቅምን በመፍጠር ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም መታቀዱንም ጠቁመዋል።፡ የኒውክለር ሃይል በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ ያግዘናል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በዚህ ዓመት 80 ዓመቱን የሚያከብረው የሩሲያ የኒውክለር ኢንዱስትሪ የሚደነቅ መሆኑን በመግለጽ ሳይንስ ከራዕይ ጋር ሲጣመር ምን መስራት እንደሚችል ሩሲያ ለዓለም አሳይታለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያም ከሩሲያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡ የሩሲያን የዘርፉን ተመራማሪዎች ከኢትዮጵያ የተማረ ሰው ሃይል ጋር በማጣመር ምሳሌ የሚሆን ትብብር በመፍጠር ለህዝብ የሚጠቅምና ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ የኒውክለር ቴክኖሎጂ ለመገንባት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም ኢትጵጵያ ተጨባጭ ሰራዎችን መስራት ጀምራለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኒውክለር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማእከል በቅርቡ እንደሚቋቋም አንስተዋል።
በመሆኑም በመተማመንና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትብብር በማድረግ እና ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የጋራ ህልማችንን ወደ ውጤት መቀየር እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል።