ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ እጅግ የተጎሳቆሉ ቤቶችን በማፍረስ የተገነቡ 253 ቤቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚገባቸዉ የሀገር ባለውለታዎች፣ ሀገር ሲያገለግሉ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ የአልጋ ቁራኛዎች፣ ጧሪ ደጋፊ ለሌላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች አስተላልፈናል ብለዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባለፈዉ እሁድ ያስተላለፍናቸው ላይ የዛሬው 253 ቤቶች ሲጨመሩ እሰከአሁን በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በ 3 ወራት ጊዜ ውስጥ ከገነባናቸው 3 ሺህ በላይ ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 924 ቤቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚገባቸው ወገኖቻችን ማስተላለፍ ችለናል ብለዋል።
ቤቶቹ የጸዱ፣ መሰረታዊ ግብአቶች የተሟሉላቸዉ፣ ዘመናዊ እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን የሚፈጥሩ፣ የራሳቸው ቅጥር ጊቢና የጋራ መገልገያዎች ያላቸው፣ የህፃናት መዝናኛና መጫወቻ እንዲሁም የንግድ ሱቆችን ያካተቱ ናቸው ሲሉም ከንቲባ አዳነች አክለው ገልጸዋል።
ይህንን የበጎ ፈቃድ ተግባር ከጎናችን ሆናችሁ ለምትደግፉ ልበ ቀናዎች እና ያስተባበራችሁ የከተማችን አመራሮች በሙሉ በተጠቃሚዎች ስም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ብለዋል ከንቲባዋ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልካም የመስቀል ደመራ በዓል በማለት የመልካም ምኞች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡