የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጫ ማህተም

You are currently viewing የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጫ ማህተም

ሀገራዊ ዕድገትን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን ማልማት እንደሚገባ ተጠቁሟል

**************************************************************************************

በዓለማችን ትንሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትጠቀም ሀብታም ሀገር ወይም ብዙ ኃይል የምትጠቀም ድሃ ሀገር የለችም፤ ይላል ‘The Energy for Growth Hub’ እ.ኤ.አ መጋቢት 7 ቀን 2023 ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡

የኃይል እጥረትን ለማስወገድ ዓለም አቀፍ ምሁራን በጥናታዊ መረጃ የተደገፉ መፍትሔዎችን የሚያመላክቱበት ማዕከል ‘The Energy for Growth Hub’ (ኢነርጂ በኢኮኖሚ እድገት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ሞተር አሊያም የደም ሥር ነው፡፡

የኤሌክትሪክ እጥረት ጉዳቱ ከግለሰብ እስከ ሀገር እና አህጉር ከፍ ያለ ነው የሚለው የምሁራኑ መረጃ፣ ለአብነትም የኤሌክትሪክ እጥረት አንድን ግለሰብ በከፍተኛ ሙያ  የመቅጠር ዕድልን ከ35 እስከ 41 በመቶ እንዲሁም በግል ስራ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆንን ከ32 እስከ 47 በመቶ እንደሚቀንስ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ እ.ኤ.አ በ2045 በአፍሪካ ካሉ ሀገራት መካከል ናይጄሪያን ብቻ በዋቢነት ብንጠቅስ ከዩናይትድ ስቴትስ የሚበልጥ ህዝብ ይኖራታል፡፡ ነገር ግን ከአሜሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም 2 በመቶውን ብቻ ለማግኘት የሚያስችል መንገድ ላይ ትገኛለች ሲል አሳሳቢነቱን ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ከድህነት ለማላቀቅ ከተፈለገ ሀገራት በተለይም አፍሪካውያን የኃይል ምንጫቸውን ሊያሳድጉና ሊያሰፉ እንደሚገባ ምሁራኑ በዓለም አቀፉ ህብረታቸው በኩል የመፍትሔ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ይህንን ዕውነት በውል የተረዳችው ኢትዮጵያም ያለፈውን፣ የአሁኑን እና በተለይም መጭውን ዘመን ታሳቢ በማድረግ ሀገራዊ ዕድገትን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ከተፈጥሮ ጋር የተስማሙ የተለያዩ የኃይል አማራጮችን በማልማት ላይ ናት፡፡

ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሐሙስ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የኒውክሌር ልማትን አስመልክቶ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም ኢትዮጵያ በቀጣይ በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ላይ በትኩረት ትሰራለች ብለዋል፡፡

በውይይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ የንቁ ወጣቶች መገኛ መሆኗን ጠቅሰው፣ ከተሞች እየዘመኑና ኢንዱስትሪዎቿም እያደጉ፣ ኢኮኖሚዋም በዓለም ፈጣን ዕድገትን እያስመዘገበ መምጣቱን አመላክተው ኢትዮጵያ በወሳኝ የዕድገት ጎዳና ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ኃይል ዘርፍ ምሳሌ ሆና መቆየቷን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለአብነትም በቅርቡ ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዘርፉ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም አስታውቀዋል፡፡

ራዕያችን ከዛሬ የተሻገረ በመሆኑ የተለያዩ የልማት አማራጮችን ተግባራዊ እናደርጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በቀጣይነት በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአብነትም ለህክምና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለውሃ አስተዳደር እንዲሁም ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ማህበር እ.ኤ.አ ሰኔ 17 ቀን 2025 የኒውክሌር ኃይል ታሪክ (The History of Nuclear Energy) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ በ1939 እስከ 45 ባሉት ዓመታት አብዛኛው ልማት በአቶሚክ ቦምብ ላይ ያተኮረ ነበር። ከ1945 ጀምሮ ግን ይህንን ኃይል ኤሌክትሪክን ለማምረት ቁጥጥር ባለው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል በትኩረት መሰራት ተጀመረ፡፡

ይህንን ተከትሎም ቀላል የማይባሉ ሀገራት የኒውክሌር ኃይልን ለልማት በማዋል ከፍታቸውን ጨመሩበት። ክንዳቸውንም አፈረጠሙበት፡፡ ለአብነትም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ሩሲያ እና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ ሀገራት የዕድገታቸው አንዱ ምስጢር ይሄው የኒውክሌር ኃይል ነው ይላል መረጃው፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ማህበር መረጃ በፈረንሣይ እ.ኤ.አ ከ1970ዎቹ አካባቢ የአንድ በርሚል የነዳጅ ዋጋ በአምስት እጥፍ ጨመረ፡፡ ይህንን ተከትሎ በሀገሪቱ ከፍ ያለ ድንጋጤን ፈጠረ፡፡ ከዚህ ድንጋጤ በኋላም ፈረንሳይ የኃይል ነፃነቷን ለማስጠበቅ እና የተረጋጋና ዝቅተኛ ዋጋ ያለው ኤሌክትሪክ ለማቅረብ በመንግስት የሚመራ የኒውክሌር ኃይል ግንባታን በስፋት ጀመረች፡፡

መንግስት የተከተለውም ይህ አዋጭ ፖሊሲ ፈረንሳይ 70 በመቶ የሚሆነውን ፍጆታዋን ከኒውክሌር ጣቢያዎቿ እንድታገኝ አስቻለ፡፡ ይህ ኃይል በፈረንሳይ የኢንዱስትሪ ኤሌክትሪክ ዋጋን ማረጋጋት፣ ኢነርጂ-ተኮር ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ፣ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲጨምር በማድረግ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ተወዳዳሪነትና ብልፅግናዋን ከፍ አደረገ፡፡

ደቡብ ኮሪያም እ.ኤ.አ ከ1970 እስከ 2000ዎቹ ባለው ጊዜ ውስጥ አስተማማኝ፣ በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ዋጋ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጭ መላክን ታሳቢ ያደረገ የኒውክሌር ግንባታን በትኩረት መስራት ጀመረች። ይህም የደቡብ ኮሪያ የኒውክሌር ስትራቴጂ ሀገሪቱን የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ዕድገትና መስፋፋት፣ ወጥነት ያለው የቴክኖሎጂ ፈጠራና የኤክስፖርት ዕድገት ተምሳሌትና መድረክ እንድትሆን አደረጋት ይላል ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ማህበር መረጃ፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው በበኩላቸው ያደጉ ሀገራት በታላላቅ መድረኮች ይጠቅመናል ብለው፣ ያሰቡትን አጀንዳ በሌሎች ላይ የሚጭኑበት ምስጢር አንዱና ዋናው የኢኮኖሚ ጉልበት ነው፡፡ ለዚህ ኢኮኖሚ ከፍታቸው ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅማቸው ወሳኝ ድርሻ አለው። በመሆኑም እንደ ሀገር በኢኮኖሚ ከፍ ብሎ ለመታየት ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኃይል ግድ እንደሚል ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለብልፅግናዋ ከፍታ አስተማማኝ መሰረት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከተፈጥሮ የተወዳጁ የተለዩ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮችን በማልማት ላይ ትገኛለች፡፡ ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም የህዳሴውን ግድብ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ይፋ ካደረጓቸው አዳዲስ እና ዋና ዋና ፕሮጀክቶች መካከል የኒውክሌር ኃይል ልማትን ለሰላማዊ ዓላማ ማዋል የሚለው አንዱ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉትም መሰል የኤሌክትሪክ ኃይል ኢንዱስትሪን ከፍ በማድረግና በማስፋፋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ዕድገትን በማጎልበት እና አጠቃላይ የኑሮ ደረጃን በማሻሻል ለሀገር ብልጽግና ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የሀገር ኢኮኖሚያዊ አውታሮች በብቃት እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል፤ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን በመፍጠር ድህነትን ይቀንሳል፤ ኢንቨስትመንትን ይስባል፤ ይህ ሁሉ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል። በመሆኑም የኒውክሌር ኃይልን የመሳሰሉ አዋጭ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮችን መጠቀም በኢኮኖሚ የጠነከረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ያግዛልም ብለዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የኒውክሌር ኃይል አተሞች ለሁለት እና ከዚያ በላይ ተሰባብረው (ኒውክለስ) ሲብላሉ የሚለቁት ኃይል ነው። በመሆኑም በመላው ዓለም ኒውክሌርን በማብላላት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የተለመደና አዋጭ መንገድ ነው፡፡

ተሰባብረው የተብላሉት አተሞች በሚለቁት ሙቀት የሚፈላው ውሃ እንፋሎት በመፍጠር ተርባይኖችን እና ጀነሬተሮችን በማንቀሳቀስ ኤሌክትሪክ ይመረታል። የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ (ኒውክሌር ፕላንት) አብላልቶ ሙቀት ለማምረት ‘ዩራኒየም-235’ የተባለውን ንጥረ ነገር እንደ ነዳጅ እንደሚጠቀም ዓለም አቀፉ የኒውክሌር ማህበር መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኒውክሌር ኃይል እንደ ሌሎች ታዳሽ ኃይሎች ሳይሆን በቀን ለ24 ሰዓታት የአየር ንብረት ሁኔታ ሳይበግረው ኃይል የማመንጨት ብርቱ አቅም እንዳለው የሚጠቅሰው የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ማህበር መረጃ በአንድ ኪሎ ግራም ዩራኒየም የሚመረት የኒውክሌር ኃይል በከሰል ከሚመረተው ኃይል በ20 ሺህ እጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡

ከዓለም ከፍተኛ የኒውክሌር ኃይል በማምረት ቀዳሚዋ ሀገር አሜሪካ ስትሆን፤ የኒውክሌር ኃይል ከአጠቃላይ የኃይል አቅርቦቷ 19 በመቶውን ይሸፍናል። ፈረንሳይ ከቻይና በመቀጠል የዓለም ሦስተኛዋ ከፍተኛ ኒውክሌር ኃይል አምራች ስትሆን፤ ከአጠቃላይ የኃይል አቅርቦቷ 70 በመቶ በላይ ኃይሏን ከኒውክሌር ኃይል በማግኘት ቀዳሚዋ ሀገር ናት። የኒውክሌር ኃይል ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው ሩሲያ የዓለም አራተኛ የኒውክሌር ኃይል አምራች ሀገር ስትሆን 36 ማብላያ ጣቢያዎች አሏት። በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ደቡብ ኮሪያ ደግሞ 26 ማብላያ ጣቢያዎች ሲኖሯት አንድ ሦስተኛውን የኤሌክትሪክ ፍጆታዋንም ከኒውክሌር ኃይል ታገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ማለትም ለኃይል አቅርቦት፣ ለምርምር፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪ እና ለአካባቢ ጥበቃ መጠቀም ያስችላት ዘንድ እ.ኤ.አ ከ1957 ጀምሮ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) አባል መሆኗን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

#Diplomacy

#Power

#Economy

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review