የቱሪዝሙ ንጋት ነፀብራቅ

You are currently viewing የቱሪዝሙ ንጋት ነፀብራቅ

 ሠው ሠራሽ ግድቦች በዓለም ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ላይ የማይተካ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ                                             

ከቀንም ቀን አለው፡፡ አንዳንድ ቀናት ታሪክ የሚዘክረውን ሁነት እና ዕውነት ያስተናግዳሉ፡፡  ከዓመት ዓመትም ከታሪካዊው ሁነት ጋር አብረው ይታወሳሉ፡፡ ጷጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተበሰረው ታላቅ ብስራት፤ የጷጉሜን 4ኛ ቀን ከቀኖች ልቃ እንድትታወስ አድርጓታል፡፡ ምክንያቱም፤ በዚህች ቀን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ በይፋ የተመረቀበት ታላቅ ሁነት ዕውን ሆኗል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሚገኙ ጉባ እና ሰዳል ተራሮች መካከል የተገነባው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ማጠናቀቂያው ድረስ በነበሩት ዓመታት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን፤ “የደም፣ የላብ፣ የእንባ ጠብታን” ጨምሮ ያላቸውን ሁሉ ከፍለውበታል። አሁን ላይ ውድ ዋጋ ከከፈሉለት ታላቅ ፕሮጀክት ፍሬ መጠቀም ጀምረዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ብርሃን ከመስጠት የተሻገረ ጥቅምን እንደሚያስገኝ በጥናትም በተጨባጭ ውጤትም የተረጋገጠ ሀቅ ነው፡፡ ለአብነት ከግድቡ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በቀጠናው ላሉ ሀገራት ጭምር እንደሚሰራጭ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃው ዕለት ባደረጉት ንግግር መግለፃቸው ይታወሳል፡፡ የግድቡ መጠናቀቅ ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡ በተለይ በአፍሪካ አህጉር ደረጃ በግዝፈቱ ቀዳሚ የሆነውን ግድብ ጀምሮ ፍፃሜ በማድረሱ ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን፤ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉባ ተገኝቶ ይህን ታሪክ እና ገድል ማየት ይገባዋል፡፡ ይህን የትውልድ ገድል ሁሉም መመልከት አለበት”  በማለት ግድቡን እንዲጎበኙ አበረታተዋል፡፡

ከጉባ ተራራ ራስ ላይ የተበሰረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፍፃሜ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም መነጋገሪያ ለመሆን ጊዜም አልፈጀበት፡፡ ቅስቀሳም አልፈለገም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁትንና ሰፊ ተደራሽነት ያላቸውን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ጨምሮ የዕለቱ ቁልፍ አጀንዳቸው አድርገውት ውለው፤ አድረዋል፡፡ የዲጂታል ሚዲያውም በተመሳሳይ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (Great Ethiopian Renaissance Dam- GERD) የሚለው ስያሜና እሱን የተመለከቱ መረጃዎች ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ፤ የሚታወቀውን የኢትዮጵያውያን ግዙፍ ፕሮጀክት የበለጠ እንዲታወቅ ዕድል ፈጥሮለታል። መታወቁ ደግሞ፤ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉባ ተገኝቶ ይህን ታሪክ እና ገድል ማየት ይገባዋል” በሚል ለኢትዮጵያዊያን በመሪያቸው አማካኝነት የተላለፈውን ጥሪ አድማስ በማስፋት ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚዳረስ የሕዳሴ ግድብን የመጎብኘት ስሜትና ፍላጎትን እንደሚያነቃ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ በቅርበት የሚሠሩ ምሁራንና ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ደመቀ ክብሩ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፤ የአንድ ግዙፍ ፕሮጀክት መፈፀም ብቻ ተደርጎ የሚወሰድ አለመሆኑን ያነሳሉ። አያይዘውም፤ የግድቡ መጠናቀቅ ለእሳቸው ያለውን ትርጉም ሲገልፁ፤ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከጨለማ የምንወጣበት ብርሃን የምናይበት ነው። ሕዝቦችን ያስተሳሰረ የአንድነታችን ምልክትም ነው፡፡ አንድ ስንሆን ምን መሥራት እንደምንችል ለዓለም ያሳየ ነው፡፡ የትውልዱ ሕልም የተፈፀመበት ፕሮጀክትም ነው፡፡ ይህ ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያወርሰው ስጦታ ነው፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ለበለጠ ሥራ የሚነሳሳበት ነው” በማለት ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሀገር ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መካከል አንዱ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የሚያመጣው ትሩፋት እንደሆነ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ደመቀ ክብሩ ጠቁመዋል፡፡ የሚከተለውን ማብራሪያም ሰጥተዋል፤ “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ነው፡፡ የዚህ ፕሮጀክት ትልቅነት፣ ያለበት መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ፣ የግንባታው የምህንድስና ጥበብ፣ የፈጠረው አዲስ ገፅታ እና ሌሎች ጉዳዮች ግድቡ ለቱሪዝም መስህብነት የላቀ አቅም እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በዚህ ግድብ ማዕከላዊ ውሃማ አካላት ላይ የሚፈጠሩ የተለያዩ ሠው ሠራሽ ደሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ደሴቶችም ጎብኚዎችን በመሳብ አስተዋጿቸው ከፍ ያለ ነው፡፡”

መምህሩ አያይዘው ፤ “ሠው ሠራሽ ግድቦች በዓለም ቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ላይ የማይተካ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። የአካባቢ ጥበቃ ውጤታማነትን ያሳድጋሉ፡፡ የውሃማ አካላት ሥነ ሕይወትን ይጠብቃሉ፡፡ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓይነት ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ ከአካባቢና ከማህበረሰብ ጋር ያላቸው መስተጋብር  ጤናማ እንዲሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ ይሠራል፡፡ ይህም በግድቦች አካባቢ ያለው ተፈጥሯዊ ሃብት እና ማህበረሰባዊ እሴት እንዲጠበቅ ያግዛል። የአካባቢው ማህበረሰብም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ያሳድጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለቱሪዝም ዕድገት እና ከቱሪዝም ጋር ተያይዞ የሚመጡ የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ የአስጎብኚ እና መሰል አገልግሎቶችን ያስፋፋል፤ ያጎለብታል።  ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ያነቃቃል”  በማለት በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምሁራዊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ በሠው ሠራሽ ግድብ የቱሪስት መዳረሻ ማዕከልነት በቀዳሚነት ሊያስቀምጠው የሚችል አቅምን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መያዙን ያነሱት የታላቅ ኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶች ማሕበር ቦርድ አባል አቶ ናሆም አድማሱ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የቱሪዝሙ ዘርፍ ላይ የሚያመጣው ውጤት ከፍተኛ ነው፡፡  በግድቡ ላይ የተፈጠረው ሠው ሠራሽ ሀይቅ (ንጋት ሀይቅ) በጣም ሰፊ የሚባል ነው፡፡ ይህም በኢትዮጵያ የውሃ ላይ ቱሪዝምን በስፋት ለመተግበር ዕድልን ይፈጥራል፡፡ በውሃ ላይ የጀልባ መንሳፈፍ እና ጉብኝትን በስፋት ማካሄድ ያስችላል፡፡ በሀይቁ ውሃ ላይ እየተዘዋወሩ ደሴቶች የሚጎበኙበትን መልካም አጋጣሚም ይፈጥራል፡፡ የስፖርት ቱሪዝም ማከናወኛም ይሆናል። በግድቡ ሥራ ላይ የተተገበረውን የምህንድስና ዕውቀት፣ ጥበብና ክህሎት እንደ አንድ የጉብኝት ፓኬጅ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥናትና ምርምር ማድረግ የሚፈልጉ ተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ወደሥፍራው የሚመጡበት አጋጣሚ ይጨምራል፡፡ የሀገር ገፅታን ያስተዋውቃል፤ ይገነባል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና ለአገልግሎት መብቃት ብቻውን ተጠባቂውን  የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገትና ጥቅም እንደማያመጣ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ተመሳሳይ ጭብጥ ባለው ሃሳባቸው አረጋግጠዋል፡፡ ግድቡ ይዞት ከመጣው የቱሪዝም ዕድል በአግባቡ ለመጠቀም እንደሀገር መሠራት የሚገባቸው ወሳኝ ተግባራት ስለመኖራቸው አንስተዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ናሆም አድማሱ፤ “ይህንን ትልቅ የቱሪዝም ሀብት ወደገበያ ይዘን ከመቅረባችን በፊት በሁሉም መስክ በቅድሚያ መሠራት ያለባቸውን ተግባራት ጥንቅቅ አድርጎ መሥራት ይገባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ለጉብኝት መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮች መሟላት ይኖርባቸዋል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት ማሟላት ያስፈልጋል። ለጎብኚዎች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን (ሆቴሎችን፣ ባንኮችን፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን…) በበቂ ሁኔታ ማቅረብ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመንግስት በተጨማሪ፤ ባለሀብቱ መዳረሻውን በማልማት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባትና ወደሥራ በማስገባት፣ በማስተዋወቅ … የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት”

ሌላኛው የዓድዋ ድል ተደርጎ የሚቆጠረውን፣ የዚህ ትውልድ መጠቀሚያ እና መዘከሪያ ሐውልት ከሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ ሀገር የሚያስገኘውን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ከወዲሁ ሊሠሩ ስለሚገባቸው ተግባራት በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና የሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ደመቀ ክብሩ አንድ ሁለት በማለት ቆጥረው አስቀምጠዋል፡፡ እንደሳቸው ምሁራዊ ዕይታ መሰረት፤ የግድቡን የቱሪዝም አቅም ለመጠቀም እንደ ሀገር አምስት ቁልፍ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት፤ ቱሪዝምን የመስክ ዕቅድ አና ዘመቻ ላይ መሥራት ነው። ይህም ማለት፡- የግድቡ ሐይቅ (ንጋት ሐይቅ) የታችኛው ክፍል ያሉ የቱሪዝም ሥፍራዎችን ማስተካከል፣ በመሰረተ ልማት እና በአገልግሎት ማሟላት ይገባል።

ስለግድቡ ለጎብኚዎች የሚሆን የተደራጀ መረጃ ማዘጋጀት፣ ማሰራጨትና ተደራሽ ማድረግ ሌላኛው ሥራ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፤ የግድቡን ንድፍ፣ አወቃቀር፣ አሠራር እና መሰል ጉዳዮች ከሣይንሳዊ እሳቤ አንፃር የተተነተነ መረጃ መዘጋጀት እንደሚገባ ገልፀዋል። የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲሆን መሠራት አለበት፡፡ በሦስተኛነት መሠራት የሚገባው ደግሞ ከግድቡ ጋር ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቱሪዝምን የማቆራኘት ተግባር እንደሆነ አንስተዋል። ከግድቡ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የቱሪዝም ሥፍራዎችን፣ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ ሁነቶችን … አስተሳስሮ መጠቀም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት የሚያሻው ስለመሆኑ አልሸሸጉም፡፡

አክለው እንዳብራሩት፤ የኢኮ-ቱሪዝም ዕድገት የሚሳለጥበትን መንገድ መፍጠር በአራተኛነት የሚነሳ ቁልፍ ጉዳይ ነው። በአምስተኛ ደረጃ፤ በአካባቢው ያለው ማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ግድቡን እና የግድቡን አካባቢ በእኔነት ስሜት እንዲንከባከበው እና እንዲጠብቀው በዘላቂነት የሚጠቀምበትን ሁኔታ ማመቻቸት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በመጨረሻም፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነቱ ባሻገር ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅም አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጣ ቁልፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን በመገንዘብ፤ ይህንን ጥቅም ለመቋደስ ግድቡን በአግባቡ ማስተዳደር እና በሣይንሳዊ መንገድ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የግድቡ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻነት ሕልም በተግባር እንዲገለፅ ኢትዮጵያዊያን ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባ፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት እና የጋራ ሀብት የሆነውን ይህንን ግድብ መጎብኘት ከማንም በፊት የኢትዮጵያዊያን መሆን እንዳለበት እንዲሁም በዚህ ትልቅ ፕሮጀክት የጉብኝት ልምዳችን ለማሳደግ መጠቀም እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review