የመስቀል ዘገባ ትውስታዎች በውጭ መገናኛ ብዙኃን

You are currently viewing የመስቀል ዘገባ ትውስታዎች በውጭ መገናኛ ብዙኃን

ኢትዮጵያ የህብራዊ ባህሎችና ሃይማኖቶች ሀገር ነች፡፡ ከዚህ ህብራዊነት የመነጩ በርካታ እሴቶች አሏት፡፡ እነዚህ እሴቶች ኢትዮጵያውያንን በህብረት ያስተሳሰሩ፣ የእርስ በእርስ መተማመንን ማሳደግ የቻሉና ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስጠብቃ እንድትቆይ ጉልህ ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ካበጃጁ ነባር እሴቶች መካከል አንዱ መስቀል ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ መስቀል ነው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የመስቀል በዓል መልከ ብዙ ገጽታዎች ተሰጥቶት ይከበራል፡፡ በዚህ በዓል የተራራቁ ቤተሰቦች በዓሉን አስታክከው ይጠያየቃሉ፡፡ ቅራኔ ውስጥ የነበሩ ሰዎች እርቀ ሰላም ያወርዳሉ፡፡ እንዲሁም ልጄን ለልጅህ የሚባባሉበት በዓልም ነው፤ የመስቀል በዓል፡፡ ይህም መስቀል ከሃይማኖታዊ ዳራው ባሻገር ከማህበረሰቡ ትውፊቶች ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው አመላካች ነው፡፡ በዚህ ዓምድም በተለይ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር ከዚህ ቀደም ምን ዘገቡ የሚለውን በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡

የመስቀል ሌላኛው ገጽ

የመስቀል በዓል ታሪካዊ ዳራው ሃይማኖታዊ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያውያን ግን እንደየአካባቢያቸው ወግና ልማድ ያከብሩታል፡፡ መስቀል ከኃይማኖታዊው በዓል ባለፈ በተለያዩ ማህበረሰቦች ዘንድ በባሕላዊ ይዘቱ ይከበራል፡፡ ይህ ኃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊት የሚስተዋልበት በዓል የውጭ ሀገር ዜጎችን ቀልብ መግዛት የቻለ ሆኗል። በዚህም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ኹነኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በሚያስተዋውቅበት “ዩኔስኮ አይሲኤች” (UNESCO ICH) ገጸ ድር ላይ ስለ መስቀል በዓልና አከባበር አስመልክቶ ባሰፈረው ጥናታዊ ጽሁፍ፣ “እንደ መስቀል ያሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት አብዛኛው ህዝቦቿ በጋራ የሚያከብሯቸውና እርስ በእርስ የሚያስተሳስሯቸው ናቸው፡፡ መስቀልም ሀይማኖታዊ በዓል መሆኑ ቢታወቅም የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች በየራሳቸው ባህል፣ ትውፊትና እምነት አካሄድ ነው የሚያከብሩት፡፡” ሲል በዓሉ ካለው ሃይማኖታዊ ፋይዳ ባሻገር በርካታ ማህበራዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አስፍሯል፡፡

በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የመስቀል በዓል አከባበር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የማህበረሰቡ ወግና ልማድ በስፋት የሚንጸባረቅበት በዓል ነው፡፡ ሙሽሮች ሰርጋቸውን በመስቀል በዓል ይፈጽማሉ፡፡ ሩቅ ይኖር የነበረ ወዳጅ ዘመድ ለመስቀል ተገናኝቶ ይጠያየቃል፡፡ ስለዚህ መስቀል የተኳረፉ የሚታረቁበት፣ የተቸገሩ ድጋፍ የሚያገኙበት በዓል ነው። በአጠቃላይ መስቀል በኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ወግና ልማዱ፤ ትውፊቱና ዕሴቱ ጎልቶ የሚንጸባረቁበት አመታዊ ክብረ በዓል ነው፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የመስቀል በዓል አከባበር ከኢትዮጵያውያን አልፎ የአለም ቅርስ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ መስቀል በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል።

በተለይ መስቀልን በድምቀት የሚከበርበት ወርሃ መስከረም ብዙ የውጭ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ነው፡፡ እንዲሁም እንደ መስቀልና ኢሬቻ ባሉ በዓላት ምክንያት ኢትዮጵያውያን ጭምር ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ የሚንቀሳቀሱበትና ጉብኝት የሚያደርጉበትም ነው፡፡ ከዚህ አንጻር መስቀልን ለማክበር የመጡ የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች እግረ መንገዳቸውን የመጎብኘት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መስቀል ቱሪስቶችን ኢትዮጵያ እንዲመጡ የሚያደርግ ትልቅ በዓል ነው።

የዝግጅት ክፍላችን የተመለከታቸው የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ ቱሪስቶች የመስቀል በዓልን ለማክበር በሚመጡበት ወቅት ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ ባሻገርም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ስለ ኢትዮጵያ በጎ ምስል ይዘው እንዲመለሱ ያደርጋል። የኢትዮጵያን ጉብኝታቸው ለሌሎችም ስለሚያጋሩ ተጨማሪ ቱሪስቶች እንዲመጡ ዕድሎችን ያመቻቻል፡፡ ከዚህ አንጻር የመስቀል በዓል መልከ-ብዙ ፋይዳ እንዳለው መመልከት ይቻላል፡፡

መገናኛ ብዙሃን ስለመስቀል በዓል

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ የሆነው የመስቀል በዓል አከባበር የውጭ ሀገር መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተው እየዘገቡት ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ታዳሚ ያላቸው መገናኛ ብዙሃን መስቀልን ከዜና ሽፋንነት ባሻገር በፎቶ ዘገባ ጭምር ሽፋን በመስጠት ላይ ናቸው፡። በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የመስቀል በዓል እንዴት እንደተከበረም በፎቶ ዘገባ ለዓለም ማህበረሰብ አድርሰዋል። ውድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ አንባብያን ከታች የተጠቀሱት የጊዜ አቆጣጠሮች በሙሉ በአውሮፓውያን የጊዜ አቆጣጠር መሆናቸው ከወዲሁ ለመግለጽ እንወድዳለን፡፡

የካናዳው የቴሌቪዥን ጣቢያ “ሲቢሲ ኒውስ” (CBC News) በመስከረም 27 ቀን 2007 “Meskel festival lights up Ethiopia” በሚል ርዕስ ስለመስቀል አከባበር ዘግቧል፡፡ “በድምቀት የሚከበረውን የመስቀል በዓልን ለማክበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በመዲናዋ አዲስ አበባ በሚገኘው መስቀል አደባባይ ተሰባስበዋል፡፡ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የተውጣጡ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን በዝማሬና በእልልታ በመዘመር ትዕይንቱን ይበልጥ ደማቅ አድርገውታል፡፡ የመስቀል በዓል የሚከበረው የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በተከበረ ማግስት ነው፡፡ ይህም ማለት ዝናባማው የክረምት ወራት አብቅቶ ብርሃናማው ወራት ጅማሮ ላይ የሚከበር በመሆኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ስሜት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። መስቀል አደባባይ እየተከበረ ባለው በዚህ በዓል ላይ፣ በዓሉን ታድሞ ያገኘነው ወጣት ሰለሞን ድጋፌ ለሲቢሲ ኒውስ እንዲህ ብሏል፤ ‘ይህ በዓል የኢትዮጵያ ህዝቦች የእርስ በእርስ መፈቃቀራቸውንና መተሳሰራቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ነው። ይህ ቀን ለኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ቀን ነው’ ብሏል” በማለት ሲቢሲ ኒውስ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

የእንግሊዙ ታዋቂ ጋዜጣ “ዘ ጋርድያን” ‘Ethiopia: Fireworks and flowers prevail as capital marks the festival of Meskel’ በሚል ርዕስ በጥቅምት 5 ቀን 2010 ባወጣው ዘገባ፣ የመስቀል በዓል አከባበር “እጅግ አስደናቂና ውብ ትዝታን የሚተው በዓል ነው” በማለት አስነብቧል፡፡ “መስቀልን ለማክበር የበዓሉ አክባሪዎች ነጭ ልብስ ለብሰው በየጎዳናው ሲንቀሳቀሱ፣ ሲዘምሩና ሲጫወቱ በዓሉን ለመታደም የመጣ የውጭ ዜጋ ሳይቀር የበዓሉ ድባብ ይጋባበታል፡፡ … በታክሲ ጓደኛዬ ወደ ሚገኝበት ሀያት አካባቢ እየተጓዝኩ የመስቀል በዓል ምን ያህል ትልቅ በዓል እንደሆነ ማስተዋል ችያለሁ። የፒራሚድ ቅርጽ የሚመስሉ ደመራዎችን በየመንገዱ ተሰርተው አይቻለሁ፡፡ ኋላም ላይ እነዚህን ደመራዎች የበዓሉ አክባሪዎች ተሰባስበው ሲያቃጥሉ (ሲያበሩ) ተመልክቻለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ በበዓሉ አክባሪዎች ፊት ትልቅ ደስታ ይታያል፡፡ ልጆችም በችቦው ዙሪያ ይጫወታሉ፡፡ ይሄ የበዓሉ ትዕይንትም ለታዳሚያን መቼም የማይዘነጋ ትዝታን ትቶ የሚያልፍ ኩነት ነው” ሲል ጋዜጣው አትቷል፡፡

ሌላው ስለ መስቀል በስፋት ያስነበበው ሮይተርስ ነው፡፡ “Ethiopians mark festival of finding Jesus’ cross” በሚል ርዕስ በመስከረም 27 ቀን 2016 ሮይተርስ በሰራው ዘገባ፣ “የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች በኢትዮጵያ የክርስትና ባህል ውስጥ ካሉት ቅዱሳን በዓላት አንዱ የሆነው የመስቀል በዓል ለዓመታት ሲያከብሩ ቆይተዋል፡፡ የመስቀል በዓልን ለማክበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ካህናትና ዘማሪዎች ነጭ ካባ ለብሰው በመዲናይቱ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይገኛሉ። በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብም በዓሉን ለማክበር ከቤቱ ይወጣል፡፡ በደማቅ አልባሳት የተዋቡ የበዓሉ አክባሪዎች ፊት ላይ ደስታ ጎልቶ ይነበባል” በማለት፤ ሮይተርስ ስለመስቀል አስነብቧል፡፡

ቢቢሲ በመስከረም 27 ቀን 2018 “Ethiopia’s Meskel festival: Bonfires, robes and crosses” በሚል ርዕስ ረዥም ሃተታ ስለ መስቀል በዓል አከባበር አስነብቧል፡፡ እንዲህ በማለት ሃተታው ይጀምራል፤ “የኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት የመጀመሪያው ትልቅ በዓል መስቀል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት አስተምህሮ ተከትሎ የሚከበረው የመስቀል በዓል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ከተደበቀበት ለመፈለግ ከተደረገው ሃሰሳ ጋር የተያያዘ ነው” በማለት የመስቀልን ታሪካዊ ዳራ ያብራራል፡፡

ቢቢሲ ከላይ በተጠቀሰው ዘገባው “በተለይ ደመራ በመባል የሚታወቀውን የበዓሉ ዋዜማ  በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ መሃል በሚገኘው መስቀል አደባባይ በመገኘት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያከብሩታል፡፡ ኢትዮጵያውያን እጅግ ያማረ አልባሳት ለብሰው በዚህ የመስቀል አደባባይ ይሰባሰባሉ፡፡ የተለያዩ ዝማሬዎችን በመዘመር እጅግ ያማረ ድባብ በታዳሚው ላይ ይፈጥራሉ” በማለት የመስቀልን ሕብረ-ባህላዊ ገጽታውን ዳስሷል፡፡

የመስቀል በዓል አከባበርን በሚመለከት ሰፊ ሃተታ ያስነበበው ሌላኛው ሚዲያ ደግሞ “WordPress.com” ነው። በፈረንጆቹ መስከረም 13 ቀን 2020 “Meskel Celebration in Ethiopia” በሚል ርዕስ ባስነበበው ሰፊ ሃተታ፣ ንግሥት እሌኒ “ሕዝቦቿ እውነተኛው መስቀል የተቀበረበትን ጢስ ያመለከተ ትልቅ እሳት እንዲያቃጥሉ አዘዘቻቸው። እነሱም እንደተባሉት አደረጉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተደበቀበት ለመፈለግ ነው ደመራ ደምረው ያቀጣጠሉት፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህንን ትውፊት መነሻ በማድረግ ነው በመስቀል ዋዜማ ደመራ ደምረው የሚያቀጣጥሉት፡፡ መስቀልን በደመቀ መልኩ የሚያከብሩትም ለዚህ ነው” በማለት፤ ስለ መስቀልና ኢትዮጵያውያን መስቀልን ለምን እንደሚያከብሩት ጽፏል፡፡

“What is Ethiopian Orthodox Meskel celebration?” በሚል ርዕስ “TRT Africa” በፈረንጆቹ መስከረም 28 ቀን 2023 በሰራው ዘገባ ደግሞ፣ በኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ መስቀል መሆኑን ያብራራል፡፡ የመስቀል በዓል የሚከበርበት ታሪካዊ ዳራው በማብራራት የሚጀምረው ዘገባው፣ “በመስቀል በዓል ዋዜማ ምእመናን በየመንገዱና በየቤተ ክርስቲያኑ አደባባዮች ላይ ደመራ ደምረው ያቀጣጥላሉ፡፡ ደመራውን ከበው መንፈሳዊ ዝማሬዎችን የሚዘምሩ እንዳሉ ሁሉ፤ መስቀልን እንደየ ባህላቸው የሚያከብሩ ማህበረሰቦችም አሉ” በማለት ስለ መስቀል ያትታል፡፡

እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የዳሰስናቸው ናቸው።ይህ የአደባባይ በዓል የበለጠ ደምቆ እና ፈክቶ እንዲታይ በመዲናዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት አበርክቶው ትልቅ ነው፡፡ ባማሩ ጎዳናዎች እና አደባባዮች ማክበር እሴቱ የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣ እና ዓለም ሀብቱን በሚፈለገው ልክ እንዲረዳው የሚያደርግ ነው፡፡ አዲስ አበባን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከተሰሩ ስራዎች መካከል ኮሪደር አንዱ ስለመሆኑ ስራው ህያው ምስክር ነው፤ መልካም በዓል!

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review