የአዲስ ህይወት በር

You are currently viewing የአዲስ ህይወት በር

          •  የነገዋ የሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል 1 ሺህ 692 ሴቶችን በተለያየ ሙያ በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲሰማሩ አድርጓል

እሴቶቻችን የአብሮነታችን እና የአንድነታችን ስንቆች መሆናቸው የመስቀል በዓል አንድ ማሳያ ነው፡፡ የእምነቱ አስተምህሮ እንደሚናገረው፣ ንግስት ኢሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ወጥታለች ወርዳለች፤ ፈተናዎችንም ተጋፍጣለች፤ በመጨረሻ ግን የልቧን መሻት እውን ማድረግ ችላለች፡፡ ሰዎችም ህልማቸውን መኖር የሚችሉት የሚያጋጥማቸውን ፈተና በጽናት መሻገር ሲችሉ ነው፡፡ በሂደቱ የሚያጋጥሙ እድሎችንም ሳያባክኑ መጠቀም የግድ ይላል፡፡

በዚህ ጽሁፍ በብርቱ ከተፈተኑ እና በ“ለነገዋ የሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል” ነጋቸው ላይ ተስፋ እና ብርሃን ከፈነጠቀላቸው መካከል የወጣት ሃሴት ሀብታሙን (ለዚህ ጽሁፍ ስሟ የተቀየረ) የሕይወት መንገድ ለማስቃኘት ወደድን፡፡

ሃሴት የተወለደችው በድሬዳዋ ከተማ ሲሆን በወጣትነት ዕድሜዋ ያላለፈችበት አስከፊ የህይወት ገፅ የለም፡፡ የህፃንነት እድሜዋን ሳታጣጥመው፣ የእናት ፍቅርን ሳትጠግበው፤ በቅጡ ሳትስቅ እና ሳትጫወት፣ የደስታዋንም ጊዜ ሳታውቅ በ1999 ዓ.ም ስምንት ዓመት ሳይሞላት ወደ አዲስ አበባ መጣች፡፡

“እናትና አባቴ በዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ እናቴ ሰው ቤት እንጀራ እየጋገረች ታኖረን ነበር፡፡ በዚሁ ሁኔታ ላይ አባቴ አረፈ። በቤታችን አብሮን የሚኖር አንድ የስጋ ዘመዴ ሊደፍረኝ ሞከረ፡፡ እናቴም ‘አንቺ ስትደፈሪ አይኔ ከሚያይ ወደ አዲስ አበባ ሂጂ’ ብላ በመኪና አሳፍራ ላከችኝ” ስትል ከእናቷ የተለየችበትንና ወደ አዲስ አበባ የመጣችበትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፡፡ 

ዘመድም ሆነ የምታውቀው ሰው የሌላት ሃሴት፤  ከድሬዳዋ ያመጣት መኪና አውቶቡስ ተራ አወረዳት፡፡ ከዚያም “በእግሬ ወደ አብነት እየተጓዝኩ አለቅስ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ይህንን የተመለከቱ ሜክሲኮ የሚኖሩ የጎዳና ልጆች ‘እኛም እዚሁ ነው ያደግነው’ ብለው ተቀበሉኝ፤ ጠንካራ እንድሆን መከሩኝ” ትላለች፡፡ 

ህይወቷ ጎዳና ላይ ቀጠለ፤ ነገር ግን ምቾት አልባና የመከራ ኑሮ ነበር። ከአስከፊው ሁኔታ ለመውጣት መኖሪያ ቤት በቤት ሰራተኝነት መስራት እንደምትፈልግ ለጓደኞቿ ነገረቻቸው፡፡ ስራ አፈላልገውላት ህፃን ልጅ እየተንከባከበች፤ ትምህርት እየተማረች ያለ ደመወዝ ለመስራት ተስማምታ መኖሪያ ቤት ገባች፡፡ ይሁን እንጂ እየሰራች ለመማር አሰሪዎቿ አልፈቀዱላትም፡፡ ከአቅሟ በላይ በምትሰራው ስራ ደከማት፤ ወገቧንም ታመመች፤ ይህ አልበቃ ብሎም ከእለታት አንድ ቀን በአሰሪዎቿ ተደበደበች፡፡ ይህን ግን መታገስ ስላልቻለች ድጋሜ የጎዳና ኑሮ ጀመረች፡፡ 

“በፊት ከማውቃቸው ጓደኞቼ ጋር ተቀላቀልኩ፡፡ ተስፋም ቆረጥሁ። ጓደኞቼ ሲጋራ አጭሰው የጣሉትን በማጨስ፣ ጫት ሲቅሙ እየቃምኩ፤ ቀስ በቀስ ሁሉንም ነገሮች ለመድኳቸው” ስትል ወደ ሱስ ህይወት እንዴት እንደገባች ትናገራለች፡፡ 

ተምራ ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ ተስፋን የሰነቀችው ሃሴት ሸራ ወጥረው በሚኖሩበት አካባቢ ለሚኖሩ ነዋሪዎች መማር እንደምትፈልግ ነገረቻቸው። ሽመልስ ሃብቴ ትምህርት ቤት 1ኛ ክፍል አስገቧት፡፡ ነዋሪዎቹም በየተራ ምሳ እያመጡላት መማር ቀጠለች። መምህሮቿም ያበረታቷት እንደነበር አልሸሸገችም፡፡

የጎዳና ህይወት በተለይ ለሴቶች ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን ሀሴት፣ እንደ እናትና አባት የሚጠብቋት ጓደኞቿን በመኪና አደጋ እና በእስር ምክንያት ከአጠገቧ አጣቻቸው። በዚህም የ6ኛ ክፍል ተማሪ እያለች የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ተፈፀመባት፡፡ “ተረበሽኩ፣ ራሴን እንድጠላ ሆንኩ፤ ሁሉ ነገር አስጠላኝ” የምትለው ሃሴት በምትኖርበት ሸራ ውስጥ መጥተው የሚያበረታቷት መምህሮቿ ጉልበት ሆነዋት እስከ 9ኛ ክፍል እንደተማረች ትናገራለች፡፡

10ኛ ክፍል ለመማር እየተዘጋጀች እያለ ወጣትነት አሸነፋት፤ እኩያ ጓደኛዋን አፈቀረች፡፡ ትምህርትም አስጠላት፤ መማር ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸው የሚያሳድጓቸው ጓደኞቿ የሚለብሱትን ልብስ መልበስ እና የሚይዙትን ስልክ ማየት ጀመረች፡፡ ትምህርቷን አቋርጣ፤ መጨረሻ ላይ ከፍቅሯም ከትምህርቷም ሳትሆን ቀረች፡፡

ለሃሴት ትልቁ ፈተና ለፍቅር አለመታደሏ ሳይሆን ቀድሞ ይወድዳት በነበረው የፍቅረኛዋ ጓደኛ በድጋሜ መደፈሯ ነበር፡፡ በዚህ አላበቃም፤ ላልተፈለገ እርግዝና ተዳረገች፡፡ እሷም ልጇን በሆዷ ተሸክማ የጎዳና ኑሮዋን ቀጠለች፡፡ በዚህ ህይወት ልጅ ወልዶ ማሳደግ ከባድ ሆኖ ተሰማት። የአራት ወር ነፍሰጡር ሆና ከጓደኞቿም ከነዋሪውም ብር ለምና በማጠራቀም እናቷ ጋር ልትወልድ ወደ ትውልድ አካባቢዋ ድሬዳዋ ሄደች፡፡

እናቷ ጋር ለመውለድና በእናት ለመታረስ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጣ ወደ ትውልድ ቀዬዋ የደረሰችው ሃሴት ያጋጠማት ግን እንዳሰበችው አልነበረም።  “እናቴ ዲቃላ ይዘሽብኝ መጣሽ በማለት አላስገባ አለችኝ” ትላለች፡፡ የሆነው ነገር ልቧን ቢሰብረውም ተስፋ ሳትቆርጥ  በተወለደችበት አካባቢ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ደጀሰላም ተጠግታ ቆየች፡፡ ከአዲስ አበባ ይዛው በሄደችው ገንዘብ ቤት ተከራይታ ጫት በሚሸጥበት ቦታ ላይ ኦቾሎኒ በመሸጥ ኑሮዋን ትመራ እንደነበር ትናገራለች፡፡

ዘጠኝ ወር በማህፀኗ የያዘችው ልጇ ይህችን ዓለም ሊቀላቀል ምጥ መጣ። ወደ ጤና ጣቢያም ሆነ ሆስፒታል የሚወስዳትና አይዞሽ የሚላት ማንም ከጎኗ እንደሌላት ስለምታውቅ፣ ቤተሰብ መምሪያ አምቡላንስ ጋር ደውላ እንዲወስዷት አደረገች፡፡ ከ10 ደቂቃ በኋላ የአብራኳን ክፋይ ልጇን እንዳቀፈች ገልጻልናለች፡፡   

ከአጠገቧ የሚደግፋት ምንም ዓይነት ሰው የሌላት ሃሴት፤ ከሆስፒታል ልጇን አቅፋ ደሟ እየፈሰሰ የሚበላና የሚጠጣ ወደሌለበት ባዶ ቤት አመራች፡፡ ከዚህ በኋላም “ደከመኝ፣ አመመኝ፣ ሰውነቴ ተንቀጠቀጠ፣ ሰርቶ መብላትም አልቻልኩም፡፡ ተኛሁ፤ ረሃቤም ጠፋ” ስትል ሰው ኖሮት እንደሌለው በመሆኗ በጣም ተከፍታ እንደነበር ትናገራለች፡፡

ወጣት ሃሴት፤ “በወለድኩ በ11ኛ ቀኔ ብር ጨረስኩ፤ የሚቀመስ ነገር ከቤቴ ጠፋ፤ አሁንም ተስፋ አልቆረጥኩም፤ እናቴ ጋር ደወልኩ፡፡ ቤት እንደሌለች ነገረችኝ፤ ሲብስብኝ ሰው ግቢ ውስጥ ሄጄ ፀሐይ ላይ የተሰጣ ደረቅ እንጀራ ሰርቄ በላሁ” ስትልም የአራስ ቤት ረሃብ እስከ መስረቅ እንዳደረሳት ትገልፃለች፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ምግብ አስመጥታ እየበላች 40 ቀን ሲሞላት ክርስትና እንዳስነሳች የምትናገረው ወጣቷ፤ እጇን ለልመና ላለመዘርጋት ልጇን አዝላ ጫማ የማሳመር ስራ ጀመረች፡፡ ለሶስት ወርም ሰራች፡፡ ይህ ግን አልቀጠለም፡፡ ልጇ የሳንባ ምች ታመመባት፡፡ ግራ ገባት፤ ቀኑ ጨለመባት፤ ብዙ የሆነችለትን ልጇን ይዛ ወደምታውቀው ከተማ አዲስ አበባ ተመለሰች፡፡    

ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ በፊት የነበሩትን ጓደኞቿን አላገኘቻቸውም ነበር፡፡ ለዕለት ጉርስና የታመመውን ልጇን ለማሳከም እጇን ለልመና ዘረጋች፡፡ ባገኘችውም ብር ልጇን አሳከመችው፤ ዳነላትም፡፡ መንገድ ዳር ሸራ ወጥራ እየኖረች መኖሪያ ቤት እየተመላለሰች ልብስ ማጠብ ጀመረች። ለትንሽ ጊዜ እንደ ሰራችም ሌላ ችግር ተደቀነባት። ታክሞ የዳነው ልጇ በድጋሜ የልብ ቱቦ መጥበብ ታመመባት፡፡ ልጇን ለማሳከም ገንዘብ የሌላት ሃሴት ሃይማኖቷ በሚፈቅደው መሰረት በፀበልና እምነት ልጇ እንደዳነላት ትናገራለች፡፡

ያጋጠማትን ፈተና እየተጋፈጠች በአስከፊ ሁኔታ ኑሮውን ስትመራ የቆየችው፣ ከሱስ መውጣት እንዳለባት የምታምነውና ነገን ተስፋ የምታደርገው ሃሴት፤ ከነበረችበት የጭንቅና መከራ ህይወት የሚያወጣት አጋጣሚ ተፈጠረላት፡፡ ይኸውም ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን የመቀላቀል ዕድል ነው፡፡ በሚያዝያ ወር 2017 ዓ.ም ወደ ማዕከሉ ገባች፡፡

“እንደ ልጆች ስቄ፣ ቦርቄ ተጫውቼ፣ ለብሼ፣ ትምህርት ቤት ስሄድ ምሳ እቃ ይዤ አላውቅም፤ ቤተሰብ ያላቸው ሲጫወቱና ከቤተሰብ ጋር ሲያሳልፉ እኔ ጫት ስቅምና ሳጨስ ነበር፡፡ በማዕከሉ ስገባ ግን የሌለኝን ቤተሰብ አገኘሁ። ተደሰትኩ፤ ታክሜም ከህመሜ ተፈወስኩ፤ በላሁ፣ ጠጣሁ፣ ለበስኩ፣ ሁሉም ተደረገልኝ” ስትል አዲስ ህይወት እንደጀመረች ትገልፃለች፡፡ 

ወደ ማዕከሉ እንደገባችም የጤና ምርመራ ተደርጎላት፣ ለአንድ ወር ያህል የህይወት ክህሎት ስልጠና ወስዳ ከነበረችበት የሱስ ህይወት እንደወጣች የምትገልፀው ሃሴት፤ የምትፈልገውን የምግብ ዝግጀት ሙያ መርጣ ለአራት ወር እንደሰለጠነች ነግራናለች፡፡

ወጣት ሃሴት የህይወት ክህሎት ስልጠና ማግኘቷ ለራሷ ያላት አመለካከት ከፍ እንዲል፣ ትልቅ ሰው እንደሆነች እንድትረዳ እና እንድታውቅ እንዳስቻላትና በደረጃ 1 በሰለጠነችው የምግብ ዝግጅት ሙያም በተመረቀች ማግስት “አኮ ኮፊ” የስራ ዕድል ተፈጥሮላት መቀጠሯን አብራርታለች፡፡

“አዲሱ ዓመት ብዙ ፈተናዎችና ስቃይ ያሳለፍነው የእኔ እና መሰል እህቶቼ ዓመት ነው” የምትለው ሃሴት፤ በዚህ ማዕከል ገብታ ስልጠና መውሰዷ የትናንት ማንነቷን እንዳታስታውስ፣ ወደ ፊት እንድትራመድ፣ አላማ እንዲኖራትና ትልቅ ነገር እንድትመኝ በር እንደከፈተላት ትገልፃለች፡፡

ትልቅ የምግብ ባለሙያ መሆን፣ በስሟ ትልቅ ሆቴል መክፈት እና በለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የበጎ አድራጎት ስራ እየሰራች መኖር የወደፊት ህልሟ እንደሆነ ገልፃ፤ ማንነቷ እንዲቀየርና ካልተመቻቸ ህይወት ውስጥ እንድትወጣ ያደረጓትን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን አመስግናለች፡፡ 

የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች የተጋለጡ ሴቶችን ህይወት ለመታደግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቋቋመ ሲሆን፣ ከሥነ ልቦና ድጋፍ እና የጤና ክብካቤ ጀምሮ ሙያዊ ስልጠናዎችን ይሰጣል፡፡ እንዲሁም የስራ ዕድል በማመቻቸት እንዲህ አይነት የሕይወት ፈተና እያሳለፉ ያሉ ዜጎች ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈ ለሀገርና ወገን የሚጠቅሙ እንዲሆን ይደግፋል። በቅርቡም ማዕከሉ በሶስተኛ ዙር በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 810 ሰልጣኞችን አስመርቋል፡፡ በዕለቱ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ “ያለ ጥፋታቸው፣ ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር የተሸከሙ፣ ለብዙ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡና በዚህም ምክንያት እንደ ጥፋተኛ የሚወቀሱ ሴት እህቶችን ህይወት ለመቀየርና ለማሻሻል እንደሚሰራ ስራ አስደሳች የለም፡፡ የእነሱን ህይወት መቀየር ከሰራናቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ይበልጥብናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሴቶች ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የመጋለጣቸው ዋነኛ ምክንያት ድህነት እንደሆነና ይህንን ችግር ለማቃለል የከተማ አስተዳደሩ ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም አክለው ጠቁመዋል፡፡ 

ማዕከሉ በይፋ ከተከፈተ በኋላ በሶስት ዙሮች 1 ሺህ 692 ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶችን በተለያየ ሙያ በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡

ማዕከሉ በይፋ ከተከፈተ በኋላ በሶስት ዙሮች 1 ሺህ 692 ለተለያዩ ለማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶችን በተለያየ ሙያ በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡  

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review