ሕይወት የዘራበት ግንፍሌ

You are currently viewing ሕይወት የዘራበት ግንፍሌ

የወንዝ ዳርቻው የተለያዩ አገልግሎቶች ተሟልተውለት የመዝናኛ ስፍራ ሆኗል

በአዲስ አበባ ከተማ የእድገት ጉዞ ወንዞቹ በአዎንታዊና አሉታዊ መልክ ተፅዕኖ አሳርፈዋል፡፡ በከተማዋ ከ76 በላይ ትላልቅና ትናንሽ ወንዞች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ወንዞች የበርካቶች ታሪክና ትዝታ የተከተበባቸው፣ እንደአሁኑ የህዝብ ቁጥር ሳይጨምርና የመኖሪያ አካባቢ ሳይሆኑ የመጠጥ ውሃ፣ የግብርና ስራ እና የተለያዩ አገልግሎቶች ሲሰጡ እንደቆዩ ነዋሪዎቹ ይመሰክራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል መነሻውን ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ አካባቢ አድርጎ ኡራኤል አካባቢ የቀበና ወንዝን የሚቀላቀለው የግንፍሌ ወንዝ አንዱ ነው፡፡

አቶ ማሞ መለሰ ትውልድና እድገታቸው አራዳ ክፍለ ከተማ ግንፍሌ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው። የ65 ዓመቱ ጎልማሳ እንደሚናገሩት፣ በድሮው ጊዜ የግንፍሌ ወንዝ በክረምት ወቅት የእንጨት ድልድይ ተሰርቶ ነበር የሚሻገሩት፡፡ በወንዙ አካባቢም አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር መኖሪያ ቤቶች አልነበሩም፤ በደን የተሸፈነ ነበር። የወንዙ ውሃም ንፁህና ኩልል እያለ ነበር የሚወርደው፡፡ “ወንዙ ውስጥ እየገባን ብይ እና ጠጠር እናወጣ ነበር። ልብስ የምናጥበው፣ የምንዋኘው፣ ሰውነታችንንም የምንታጠበውም ወንዙ ላይ ነበር” ሲሉ ትውስታቸውን ያነሳሉ፡፡

ከጊዜ በኋላ በወንዙ ዳርቻ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን በብዛት እየሰሩ መኖር ሲጀምሩ፣ የሽንት ቤት ፍሳሽን ጨምሮ የተለያዩ ቆሻሻዎች የሚወገዱበት ስፍራ እየሆነና እየተበከለ መምጣቱን አቶ ማሞ ያነሳሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ቤቶቹ ከወንዙ ዳርቻ ተጠግተው የተገነቡ በመሆናቸው በክረምት ወቅት ወንዙ ሲሞላ በንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ያስከትል እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ሲሳይ ወልዴም ትውልድና እድገታቸው ግንፍሌ አካባቢ ነው፡፡ የግንፍሌ ወንዝ የቀደመ ገጽታ በተለያዩ ምክንያቶች እየተቀየረ መምጣቱን የገለጹት፣ “በቤቶች የተከበበና መፈናፈኛ የሌለው፣ በተለያዩ የፕላስቲክና ፍሳሽ ቆሻሻዎች  ከመበከሉ የተነሳ ውሃው ተፈጥሯዊ መልኩን ያጣ፣ መጥፎ ጠረን ያለውና ለኑሮ የማይመች አካባቢ” በማለት ነው፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደመሰከሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንና የተለያዩ ተቋማት ጥናቶችም እንደሚያሳዩት፣ የግንፍሌ ወንዝ የቆሻሻ መጣያ ሆኖ በከፍተኛ ደረጃ በመበከሉ ተፈጥሯዊ ወዙን አጥቶ፣ ሰዎች ለማየት የማይመርጡት፣ ቆሻሻ ለመጣል ካልሆነ በስተቀር ለልማት ጀርባቸውን የሰጡት ስፍራ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞችን ለመታደግ የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት የግንፍሌ ወንዝ ለምንም አገልግሎት ከማይውልበት በማውጣት ዳግም ህይወት እንዲዘራበት አድርጓል፡፡ አሁን ወንዙ ተፈጥሯዊ መልኩን ይዞ ይታያል። ይህንን ለማረጋገጥ ከአራት ኪሎ ወደ መገናኛ በሚወስደው መስመር ጥቂት ኪሎ ሜትሮች እንደተጓዝን ሺህ ሰማንያ እና ከላይኛው ቤተ መንግስት ጀርባ ያለውን አካባቢ ማየት በቂ ነው፡፡ የግንፍሌ ወንዝ የሚፈስበት ይህ አካባቢ በተፈጥሮ ድንቅ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው ሆኖ፣ የወንዙ ዳርቻ በተለያዩ አበቦች፣ አረንጓዴ ሳሮች፣ የፍራፍሬና የተለያዩ ችግኞች የተሸፈነ ነው፡፡ በወንዙ ዳርቻ ሰዎች በእግር እየተጓዙ አሊያም አረፍ ብለው ነፋሻማውን አየር እየማጉ፣ አዕምሯቸውን ዘና የሚያደርጉበት የእግረኛ መንገዶች ተሰርተዋል፤ ማረፊያ ወንበሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች የክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን ብቻቸውንና ከጓደኞቻቸው ጋር ከወንዙ የሚወጣውን የፏፏቴ ድምፅ እያደመጡ፣ የአካባቢውን ውበት እያደነቁ ሲዝናኑ ተመልክተናል፡፡

ወጣት እዮብ እንዳለን ፅዱና ውብ ሆኖ በተሰራው የግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ አረፍ ብሎ ሲዝናና ነበር ያገኘነው። አዋሬ አካባቢ በግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ከቤተሰቡ ጋር ለአስራ አራት ዓመታት ያህል መኖሩንና ለልማት ሲነሱ አሁን ላይ አራት ኪሎ አካባቢ እየኖረ እንደሆነ ይናገራል። ቀደም ሲል የግንፍሌ ወንዝ በቆሻሻ የተበከለ፣ ለማየት ደስ የማይል፣ መጥፎ ሽታ ያለውና የወንዙ ቀለምም የጠቆረ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

አሁን የወንዝ ዳርቻው አረንጓዴ ሆኖ፣ ማረፊያ ወንበሮች፣ የእግረኛ መንገድ፣ ካፌና የተለያዩ አገልግሎቶች ተሟልተውለት ለዓይን የሚስብ የመዝናኛ ስፍራ ሆኗል፡፡ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፋሽን ዲዛይን ተማሪ መሆኑን የሚናገረው ወጣት እዮብ፣ “በክረምት ወቅት መዝናኛ ቦታ እንደልብ ስለማይገኝ ብዙውን ጊዜ የማሳልፈው በቤት ውስጥ ነበር፡፡ አሁን ግን አየር እየወሰድኩ፣ ለብቻዬ በጥሞና የማሳለፍበት ደስ የሚል ስፍራ አግኝቻለሁ” ይላል፡፡   

ወጣት ቃልአብ ተስፋዬ ደግሞ ከመካኒሳ አካባቢ መጥቶ ሲዝናና ነው ያገኘነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ ከጓደኛው ጋር ሆኖ በአካባቢው ሲያልፍ ድንገት ቀልቡን ስቦት እንደተመለከተውና የእረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ ምቹ መሆኑን በመረዳት ለሁለተኛ ጊዜ እንደመጣ ነግሮናል፡፡ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተናን ወስዶ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ያለው ወጣት ቃልአብ፣ ከዚህ በፊት መፅሐፍ ማንበብ የሚወድ ቢሆንም ምቹ ቦታ ማግኘት ስላልቻለ ሰፈር ውስጥ ኳስ በመጫወት ነበር ብዙውን የእረፍት ጊዜውን የሚያሳልፈው፡፡ “መጽሐፍ ማንበብ እወዳለሁ፤ ግጥምም እፅፋለሁ። በአረንጓዴ ዕፅዋትና አትክልቶች የተሸፈነውን፣ ፅዱና ነፋሻማ አየር  ያለው ይህ ስፍራ ከራስ ጋር ለማሳለፍ ደስ የሚል ስለሆነ መርጬው ነው የመጣሁት፡፡” ይላል፡፡ 

“ወንዙ ከመበከሉ የተነሳ ዋና ዋኝቼ ቦርቄ ያደኩበትና የማውቀው አይመስለኝም ነበር፡፡” የሚሉት አቶ ማሞ፣ አሁን ግንፍሌ ፀድቶና ተፈጥሯዊ ውበቱ ተመልሶ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሲሳይም የግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ገፅታው መቀየሩን ይመሰክራሉ። በአበቦች፣ ለምለም ሳርና የተለያዩ ዕፅዋት ተሸፍኖ፣ ማረፊያ ወንበሮች፣ ካፌ፣ የእግረኛ መንገድ፣ ድልድይ ተሰርቶበት የአይን ማረፊያ ሆኗል፡፡

ባለድርሻ አካላት ምን ይላሉ?

የከተማዋን ወንዞች የማልማትና የመጠበቅ ኃላፊነት ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አንዱ ነው፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢንጂኒዬር እንዳሻው ከተማ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ የአዲስ አበባ ወንዝና የወንዝ ዳርቻዎች ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩባቸው፣ ብዙዎችም በህገ ወጥ መንገድ የሰፈሩባቸው፣ ቆሻሻ የሚጣልባቸውና የተበከሉ በመሆናቸው የከተማዋ ፀጋ ከመሆን ይልቅ ዕዳ ሆነው ነበር፡፡ ወንዞቹ የሚነሱባቸውና የሚጓዝባቸው ቦታዎች ብቻ ሳይሆን መዳረሻ በሆኑትና የግብርና ስራ በሚከናወንባቸው የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች እንዲሁም አዋሽ ወንዝ ድረስ ጉዳት ነበራቸው፡፡

ወንዞቹ የወንዝነት ተፈጥሯዊ ባህርያቸውን አጥተው የቆሻሻ መጣያ የሆኑ፤ ለጤናማ የማህበረሰብ እድገት የማይመቹ ነበሩ፡፡ ኢንጂኒዬር እንዳሻው እንደገለፁት፣ የግንፍሌ ወንዝ በመሀል አዲስ አበባ የሚገኝ ሆኖ፤ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠጋግተው የሚኖሩበት አካባቢ ነው። ከስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ተነስቶ በአዋሬ አድርጎ አጎዛ ገበያ ላይ ከቀበና ወንዝ ጋር ይገናኛል፡፡ ከሶስት ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመትም አለው፡፡

ኢንጂኒዬር እንዳሻው እንደሚገልፁት፣ የግንፍሌ ወንዝና ዳርቻ በርካታ ሰዎች የሰፈሩበት፣ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያውን የሚገኙበት በመሆኑ የተጨናነቅ፣ ከወንዝነት ይልቅ የቆሻሻ ማስወገጃ፤ ለመኖሪያነትም ሆነ ለእይታ የማይመችና ደስ የማይል አካባቢ ነበር፡፡ ማህበረሰቡም ክረምት በመጣ ቁጥር ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሚሆንበት ሁኔታም ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ኃ/ጊዮርጊስ ከላይ የተነሳውን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ግንፍሌ መሀል የከተማዋ እምብርት፤ የላይኛውን ቤተ መንግስት ጭምር ተጎራብቶ የሚገኝ ቢሆንም በወንዙ አካባቢ ለሚኖረውም ሆነ አጠቃላይ ለከተማው ህዝብ ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ ከመኖሪያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሚለቀቅና የሚጣል ቆሻሻም ለከፍተኛ ብክለት በመዳረጉ ስነ ምህዳሩና ብዝሃ ሕይወት ሀብትነቱ ተመናምኗል፡፡ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ከመሆን ይልቅ ሰው ለማየት የሚጠየፈው፣ የቆሻሻ መጣያ፣ የጎርፍና የጤና ስጋት ምንጭ ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ እና የቀበና ወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማት አስተባባሪ አቶ ሞገስ ባልቻ ሰሞኑን “ከተፈጥሮ ጋር እርቅ” በሚል ርዕስ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በተላለፈው ጥናታዊ ፊልም (ዶክመንታሪ) ላይ እንደተናገሩት፣ በግንፍሌ ወንዝ ላይ የወንዝ ዳርቻ ልማት ከመጀመሩ በፊት ወንዙ ከመበከሉ የተነሳ የነበረው መልክ የተቃጠለ ናፍጣ የሚመስል፣ መጥፎ ጠረን ያለውና ለሰዎች ጤናና ለደህንነት ስጋት የሚጭር ነበር፡፡

ይህንን የወንዙን ሁኔታ ለመቀየር እና ምቹ የመኖሪያና የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ለማስቻል የከተማዋ አመራር ቁርጠኛ የሆነ አቋም በመያዝ ወደ ወንዝ ዳርቻ ልማት ገብቷል፡፡ የግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ፅዱ፣ ውብና አረንጓዴ ገፅታን ተላብሶ መሰራቱን ያነሱት አቶ አሰግደው፣ ይህም የአካባቢው ስነ ምህዳር፣ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች እንዲጠበቁ፣ የጠፉ ዕፅዋትና እንስሳት እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡ ክረምት በመጣ ቁጥር የከተማ አስተዳደሩንና ነዋሪዎችን ይፈትን የነበረውንና በተለያዩ ጊዜያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ ሲያስከትል የቆየውን የጎርፍ አደጋ ማስቀረት አስችሏል፡፡ በወንዝ ዳርቻ ልማቱ የጎርፍ መከላከያ የድጋፍ ግንቦች ግንባታና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ኢንጂኒዬር እንዳሻው በበኩላቸው በግንፍሌም ሆነ በሌሎች የወንዝ ዳርቻ ልማት የተከናወነባቸው አካባቢዎች ከወንዞቹ ጠርዝ ግራና ቀኝ (buffer zone) ያለው 30 ሜትር ርቀት ከማንኛውም ግንባታና ንክኪ ነፃ እንዲሆኑ ተደርገው እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በማካተት ተገንብተዋል። የግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ካፌን፣ ወንዙ ንፁህና ወጥ ሆኖ እንዲፈስ የሚያችስሉ አነስተኛ የውሃ ማቆሪያዎችን፣ መፀዳጃ ቤቶችን፣ ሰዎች በእግር የሚጓዙበት ወይም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው የእግረኛ መንገዶችን፣ የልጆች ማቆያንና መጫዎቻዎችን ጨምሮ የተለያዩ ልማቶችን አካትቶ የተገነባ አረንጓዴ ልማት ነው፡፡ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችንም በአዋሬና በተለያዩ ቦታዎች በተገቢ ሁኔታ እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡

የውበትና የጥላ ብቻ ሳይሆን ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችም ተተክለውበታል፡፡ በዚህም ለእይታ የማይመችና ለጤና ስጋት የነበረው ወንዝ ወደ ፅዱ፣ ውብና የመዝናኛና ቱሪዝም ማዕከልነት መቀየር ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ልማት ሙሉ በሙሉ ግንባታው መጠናቀቁን ኢንጂኒዬር  እንዳሻው ገልፀውልናል፡፡ 

አዲስ አበባ ወንዞችን መነሻ በማድረግ የተመሰረች ከተማ ብትሆንም ወንዞቿ ተፈጥራዊ ገፅታቸውን አጥተው ነበር የቆዩት፡፡ የወንዞች መልማት፣ ወደተፈጥሯዊ መልክና ገፅታቸው መመለስ የአዲስ አበባ ትልቁ ብስራት ነው፡፡ የወንዝ ዳርቻ ልማት ወንዞችን ወደ ተፈጥሯዊ ይዘታቸው ለመመለስና ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ የከተማዋ አረንጓዴ ሽፋንም እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ አዲስ አበባ የቱሪስቶች መተላለፊያ ሳትሆን ማረፊያ እንድትሆን እንዲሁም ዜጎች ፅዱና አረንጓዴ አካባቢ የመኖር መብታቸውን ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ኢንጂኒዬር  እንዳሻው አስረድተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት የወንዝ ዳርቻ ልማትን በሰፊው ከመተግበር ባሻገር ወንዞች ንጽህናቸው   ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ የወንዝ ዳርቻ ልማትና ብክለትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ደንብ ቁጥር 180/2016 ወደ ስራ መገባቱ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ የከተማዋን ገፅታ የሚቀይር፣ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች ያሉት፣ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ልማት እንደሆነ አቶ አሰግደው አስረድተዋል፡፡

የቀበና ወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማት አስተባባሪ አቶ ሞገስ እንደተናገሩት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት በአጭር ጊዜ የአዲስ አበባን ገጽታ በትልቁ የቀየረ ስራ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት፣ የአፍሪካ ከተሞች ኩራት፣ ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የገባውን ቃል በተጨባጭ እየተገበረ ስለመሆኑ ህያው ምስክር የሆነ ስራ ነው፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review