ከአትሌቲክሱ ባለ ድሎች ምን እንማር?

You are currently viewing ከአትሌቲክሱ ባለ ድሎች ምን እንማር?

አንድ የዓለም ሪከርድና ዘጠኝ የሻምፒዮናው ሪከርድ የተሻሻለበት፣ ሳሞኣ፣ ሴንት ሉሲያ እና ዩራጓይ የተሰኙ ሀገራት በሻምፒዮናው ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ውስጥ የገቡበትና ታንዛኒያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከቀናት በፊት ተጠናቅቋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ ሀገራት ሜዳልያ ውስጥ የገቡበት ሆኖ በተጠናቀቀው 20ኛው የዓለም ሻምፒዮና ቦትስዋና በ4×400 ሜትር ወንዶች የዱላ ቅብብል ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊ ሀገር በመሆን ታሪክ ሰርታለች።

የዓለም አትሌቲክስ ገፀ ድር መረጃ እንደሚያሳየው 196 ሀገራት የተሳተፉበትና በጃፓን ቶኪዮ ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮናው 53 ሀገራት ሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡበት ሆኖ አልቋል። ከአሁን በፊት 46 ሀገራት ሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡት በ2007 የኦሳካ እና በ2023 የቡዳፔስት ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲሆን፣ የቶኪዮው መድረክ በሰባት ሀገራት ብልጫ ያለው ሆኖ ተጠናቅቋል፡፡

በኦሳካ፣ የበርሊን፣ ዴጎ፣ ሞስኮ፣ በኦሬጎን፣ ቤይጂንግ፣ ለንደን፣ ዶሃ ላይ በሜዳሊያ ብዛት የደመቀችው ኢትዮጵያ ከአዳዲሶቹ የስኬት ታሪኮች ከአንዱም ሳትቋደስ ተሳታፊዎቿ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከውጤት በራቀችበት በዚህ መድረክ የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፎ ምን እንደሚመስልና ምን አይነት ውጤት እንዳመጡ እንዲሁም ስኬታማ የሆኑ ሀገራትስ ምን ስለሰሩ ተሳካላቸው የሚሉትን ጉዳዮች መፈተሽ ደግሞ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ አፍሪካ ከሌላው ዓለም የተለየ ቦታ አላት። በተለይ በረጅም ርቀት ሩጫዎች የዓለምን መድረክ የመቆጣጠር አቅሟ ለዘመናት የታየ እውነታ ነው። በቶኪዮ በተካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም ይህ እውነታ በድጋሚ ተረጋግጧል። አፍሪካውያን አትሌቶች ከሌሎች ሀገራት አትሌቶች ጋር በነበረው ከፍተኛ ፉክክር፣ በጠንካራ ዝግጅት እና ከፍተኛ ተነሳሽነት የአህጉሪቱን ስም ከፍ አድርገዋል፡፡ ኬኒያ ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ባጠናቀቀችበት ውድድር አፍሪካ 22 ሜዳልያዎችን መሰብሰቧን የአፍሪካን ኒውስ ዘገባ ያሳያል፡፡

የደቡብ አፍሪካዊቷን ሀገር ቦትስዋና ወርቃማውን ትውልድ አስቀድመን ስንመለከት አዲስ የተጻፈ ታሪክ እናገኛለን። ቦትስዋና በቶኪዮ ሻምፒዮና ላይ ትልቅ አሻራ ጥላለች፡፡ ከዓመታት በፊት በ400 ሜትር ርቀት ላይ የነበራትን ብቃት በድጋሚ በማሳየት የአፍሪካን አትሌቲክስ ክብር ከፍ አድርጋለች። በተለይም በወንዶች የ400 ሜትር ሩጫ ኮለን ኬቢናትሺፒ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ለሀገሩ ታሪካዊ ድል አስመዝግቧል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ቦትስዋና በ4×400 ሜትር ቅብብል ውድድር ከአሜሪካና ከደቡብ አፍሪካ ጋር በነበረው ከፍተኛ ፉክክር አሸንፋ የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ከተለፋ በአጭር ርቀት ሩጫ ውድድሮችም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ማረጋገጫ ሰጥቶ አልፏል፡፡

ደቡብ አፍሪካ እንደዚሁ በቶኪዮ ሻምፒዮና ላይ ያሳየችው አፈጻጸም እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ በ4×400 ሜትር ቅብብል ውድድር ላይ ጠንካራ ብቃት በማሳየት የነሐስ ሜዳሊያ በማምጣት፣ በዓለም አትሌቲክስ መድረክ ላይ ያላትን ቦታ አጠናክራለች፡፡ አልጄሪያ በበኩሏ በ800 ሜትር ሩጫ ድጃመል ሴጃቲ በወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ከኬንያው ኢማኑኤል ዋንዮኒ ጋር ባደረገው ከፍተኛ ፉክክር የብር ሜዳሊያ አምጥቷል። ይህ በወንዶች የ800 ሜትር ሩጫ የአፍሪካ አትሌቶች ያላቸውን የበላይነት በድጋሚ ያሳየ ክስተት ሆኗል።

ኬንያ የረጅም ርቀት ሩጫ ንግሥናዋን በድጋሚ አረጋግጣለች፡፡ በቶኪዮ በተካሄደው ሻምፒዮና የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ከአሜሪካ ቀጥሎ ትልቅ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ ኬንያ በወርቅ፣ በብር እና በነሐስ ሜዳሊያ ብዛት ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ የአትሌቲክስ ልዕልናዋን አረጋግጣለች፡፡ በተለይም በሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ሩጫ ቤትሪስ ቼቤት የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ ታላቅ ስኬት አስመዝግባለች፡፡ በወንዶች የ800 ሜትር ሩጫ ኢማኑኤል ዋንዮኒ በሻምፒዮናው ታሪክ እጅግ ፈጣን ሰዓት አንዱን (1:41.86) በማስመዝገብ ለሀገሩ ወርቅ አስገኝቷል ይላል የዴይሊ ኔሽን መረጃ፡፡

ከታላላቆቹ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሀገራት ባሻገር፣ ሌሎች ሀገራትም ስኬት አስመዝግበዋል፡፡ ታንዛኒያ በቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ታሪክ አስመዝግባለች። አልፎንስ ፌሊክስ ሲምቡ በማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፎ ታሪክ ሰርቷል፡፡ ይህ ድል የታንዛኒያን ስም ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ ለአፍሪካ የማራቶን ሩጫ ያለውን ተስፋ አሳይቷል።

በሻምፒዮናው የኬንያ የበላይነት በረጅም ርቀት ሩጫ፣ በአጭርና መካከለኛ ርቀቶች የቦትስዋና መነቃቃት እንዲሁም የታንዛኒያ ታሪካዊ ስኬት አፍሪካ በአትሌቲክስ ዓለም ያላትን ቦታ ከፍ ያደረገ ስለመሆኑ ደግሞ በአፍሪካ አትሌቲክስ ጉዳዮች ፀሐፊው ዴኒስ ፒተር ያስረዳል፡፡ ፀሐፊው እንደሚለው የአፍሪካ አትሌቶች በዓለም መድረክ ላይ ያስመዘገቧቸው ስኬቶች እንዲሁ በአጋጣሚ የመጡ አይደሉም። ይልቁንስ በስተጀርባው የዓመታት ከባድ ስልጠና፣ ጠንካራ ቁርጠኝነት እና የስፖርት ሳይንስን መጠቀም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ይላል።

የዴይሊ ኔሽን ፀሐፊው ጀምስ ሚዋንባ እንደሚለው ከሆነ አብዛኞቹ አፍሪካውያን አትሌቶች ስኬትን ለማግኘት በከፍታ ቦታዎች (High Altitude) ላይ በመሠልጠን የሰውነታቸውን የኦክሲጅን አጠቃቀም አቅም አሳድገዋል፡፡ ይህ የሥልጠና ስልት በተለይም የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ለረጅም ጊዜ ሲጠቀሙበት የቆዩ እንደሆነ እሙን ነው።በአፍሪካ አትሌቲክስ ጉዳዮች ፀሐፊው ዴኒስ ፒተርም በዚህ ሀሳብ ይስማማል፡፡ ፀሐፊው እንደሚለው በተለይ እንደ ኬንያውያን ያሉ አትሌቶች አስደናቂ ብቃት ጀርባ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ጠቅሶ፣ የዚህ ስኬት መሠረታዊ ነገሮች ከዘመናት ከቆየ ባህል፣ ከተፈጥሯዊ ሁኔታዎች እና ከስልጠና ስልቶች ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በተለይም ዘመናዊ የስልጠና አሰራሮችን መዘርጋት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፎ ማሳደግ፣ ተተኪ ስፖርተኞች በብዛት ማምረት ለስኬታማነታቸው በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች እንደሆኑ ፀሐፊው ያብራራል፡፡

አብዛኞቹ የኬንያ አትሌቶች በተለይም በረጅም ርቀት የሚወዳደሩት ከባህር ወለል በላይ በከፍተኛ ቦታዎች (ታዋቂው ኢተን ከተማ በማሳያነት ብንወስድ) ላይ ይኖራሉ። አትሌቶች በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲሰለጥኑ ሰውነታቸው ከወትሮው የበለጠ ቀይ የደም ሴሎችን በማምረት ኦክስጅንን በብቃት የመጠቀም አቅሙ ይጨምራል። ይህ ደግሞ በዝቅተኛ ቦታዎች ወደሚደረጉ ውድድሮች ሲሄዱ ትልቅ ጥቅም ይሰጣቸዋል። በሌላ በኩልም በኬንያ ብዙ ወጣቶች አትሌቲክስን እንደ የኑሮ መሠረትና የመታወቂያ መንገድ አድርገው ይወስዱታል። የብዙ ታላላቅ አትሌቶች ስኬት ብዙ ወጣቶችን ስለሚያነሳሳ፣ በየቀኑ ጠንካራና የቡድን ስልጠናዎችን ያደርጋሉ። ይህ ተፎካካሪ የሆነ የሥልጠና ባህል ወጣቶች ጠንካራ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል።

የአፍሪካን አትሌቲክስ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው ይችላል በማለት ጀምስ ሚዋንባ በቀጣይም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ያለውን ጉዳይ ይገልጻል፡፡ የሀገራት መንግሥታት ለአትሌቲክስ የሚሰጡት ድጋፍ፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ማሻሻልና ወጣቶችን ከልጅነታቸው ጀምሮ ማሰልጠን፣ ለወደፊት የአፍሪካ ስፖርት መሻሻል ወሳኝ መሆኑን የቶኪዮው ሻምፒዮና አሳይቷልና ሊሰራበት ይገባል ይላል።

619 ሺህ 288 ተመልካቾች በቶኪዮ ብሔራዊ ስቴዲየም ተገኝተው ውድድሮቹን በታደሙበት 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሜሪካ በ16 ወርቅ፣ 5 ብር እና 5 የነሐስ ሜዳልያ በበላይነት ስታጠናቅቅ ኬንያ በ7 ወርቅ፣ 2 ብር 2 ነሐስ 2ኛ እንዲሁም ካናዳ በ3 ወርቅ 1 ብር እና 1 ነሐስ 3ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፡፡ ኢትዮጵያም በ2 ብር እና በ2 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 22ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት መድረክ ሆኖም ስለመጠናቀቁ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review