አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ

You are currently viewing አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ

“ህብረተሰቡና የፀጥታ ተቋማትን የማገናኘት ስራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት”

                                                  የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

ከተሞች ለስራ፣ ንግድና ቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹና ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ሁኔታዎች መካከል የተሟላ ሰላምና ደህንነት የመኖር ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ዜጎች በሰላም ወጥተው የሚገቡበትን ሁኔታ የፈጠሩ፣ ሰላምና ደህንነታቸውን ያረጋገጡ፣ ዝቅተኛ የወንጀል ምጣኔ ያለባቸው ከተሞች ለኑሮ ተመራጭ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፣ የአፍሪካውያን መናኸሪያ፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ በዓለም ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ ሰላሟንና ደህንነቷን አጠናክሮ ለማስቀጠል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በከተማዋ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል፣ ሰላም፣ ደህንነትንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ሚና እየተወጡ ካሉ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አንዱ ነው፡፡

ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረውና አንጋፈው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ሪፎርም በማካሄድ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከልና ሰላምንና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተልዕኮውን በብቃት መወጣት የሚችል ተቋም መሆን ችሏል፡፡ ከትናንት በስቲያም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የማኔጅመንት አባላት በተቋሙ በመገኘት በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በተለያዩ ጉዳዮች ያከናወናቸውን የሪፎርም ስራዎችን ጎብኝተዋል፤ ከተቋሙ አመራሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ፌዴራል ፖሊስ ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል እና ከተማዋ ደህንነቷ የተጠበቀና ዜጎቿ ያለ ስጋት የሚንቀሳቀሱባት እንድትሆን ለማስቻል የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገኙባት፣ ዲፕሎማቶች የሚኖሩባት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት የሚጎበኛት ከተማ ናት፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች፣ እየተዋበችና እያማረች በመምጣቷ ቀጣናዊ፣ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ትላልቅ ጉባኤዎች በስፋት እየተካሄዱባትና ተመራጭ እየሆነች መጥታለች፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫቸውን በከተማዋ ሲያደርጉ፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና ኮንፈረንሶች ለማድረግ ሲታሰብ አስቀድሞ ከግምት የሚገባው የከተማዋ ሰላምና ደህንነት የተጠበቀ መሆን ነው፡፡ የሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ከተማዋ ትላልቅ ጉባኤዎችን የመሳብ አቅሟ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

አሁን ላይ አዲስ አበባ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝቅተኛ የወንጀል ምጣኔ የሚመዘገብባት፣ የተሻለ ሰላምና ደህንነት ያላት ከተማ ነች፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘትም የፀጥታና ደህንነት ተቋማት፣ የህብረተሰቡና የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ቅንጅት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስም እንደ አንድ የፀጥታ አካል ተልዕኮውን ለመወጣት ባደረገው ሪፎርም የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል ህዝቡ በቀላሉ የፖሊስ አገልግሎት ሊያገኝ የሚችልበት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (EFPApp) በማልማት ስራ ላይ ማዋሉን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ተናግረዋል። መተግበሪያው ህብረተሰቡ ከፖሊስ በቀላሉ የሚፈልገውን አገልግሎት የሚያገኝበት፣ ወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ መረጃዎች የሚለዋወጥበት፣ በራሱ ፖሊስ ሆኖ አካባቢውና ከተማዋ የሚጠበቅበት ዕድል የሚፈጥር ስለሆነ መተግበሪያውን በስፋት እንዲጠቀምበት በማስተዋወቅ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ሚና የላቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህዝብና መንግስትን እንደ ድልድይ ሆኖ በማገናኘት እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን ያነሱት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፣ ወንጀልን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችና በከተማዋ ውስጥ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ልማቶች ከህዝብ ለማድረስ የሚሰራውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

“አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የከተማዋን ስያሜ የያዘ በመሆኑ በከተማዋ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ህብረተሰቡ ከምንም በላይ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት ይፈልጋል፡፡” ያሉት ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፤ ከዚህ አኳያ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚሰራቸው ስራዎች በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ተደራሽ በመሆናቸው በእውነት ላይ በመመስረት ህብረተሰቡና መንግስት፣ ህብረተሰቡና የፀጥታ ተቋማትን ማገናኘት የሚችል በጣም ጥሩ የሚባል ስራ መስራቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ እንዲሁ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ፖሊስ በሚሰራው ስራ ደጋፊ በመሆን እየሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን አንስተዋል። “የእኛ ተቋም ሰፊ ሪፎርም በማድረግ ብዙ ስኬት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በሰው ሀይል፣ በሎጂስቲክስ፣ በቴክኖሎጂና በአፈጻጸም የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝ፤ በመላ ሀገሪቱ ስምሪት ወስዶ የሚሰራ ተቋም ነው፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እኛ ለምንሰራው ስራ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ ሰላምና ፀጥታን ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ የሰሯቸውን መልካም ስራዎች ያሰራጫል፡፡ ከህዝብ የሚገኙ መረጃዎችን ለፖሊስ ያቀርባል፡፡ ታማኝና ተጨባጭ መረጃዎችን በመስጠት ጠንካራ የሚዲያ ተቋም እንደሆነ በተለያየ ጊዜ አይተነዋል” ብለዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው በፌዴራል ፖሊስ የተካሄደው ሪፎርም ስኬታማና  ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም ጥሩ ግብአት መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ከብዙ ዓመታት በኋላ አሁን ላለችበት ደረጃ እንድትደርስ የፌዴራል ፖሊስ ትልቅ ድርሻ ተወጥቷል፡፡ ተቋሙ ባደረገው ሪፎርም የተገኘውን ውጤት በተጨባጭ እያየነው ነው፡፡ ወደ ህዝብ ቀርቦ በሚሰጠው ምላሽም ተአማኒነትን እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየ ያለው ለውጥ ለሀገራችንና ከተማችን አልፎም ለቀጣናችንም የሚተርፍና ተምሳሌት የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡

“የሀገር ፍቅርን ለመማር ከፀጥታ ሀይል የተሻለ ሌላ አካል የለም” ያሉት አቶ ካሳሁን፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም እንደ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ በከተማዋ በቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ስራ መመልከት ስለሚያስፈልግ የተቋሙ አመራሮች በአካል በመገኘት ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለመዲናችን ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ መሆን አለበት። መረጃዎችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ በወቅቱ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ የአፍሪካ ዋና መናኸሪያና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል ናት። የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የከተማውን ሰላም እና ፀጥታ በማስከበርና የትራፊክ እንቅስቃሴን በማሳለጥ በኩል የሚሠራቸው ተግባራትን በመከታተል ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአራት የመገናኛ ሚዲያ አውታሮች በቴሌቭዥን፣ ሬዲዮ፣ ዲጂታልና ህትመት መረጃዎችን ለህብረተሰቡ እያደረሰ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ ካሳሁን፣ በፌዴራል ፖሊስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል ለህዝቡ መረጃ ተደራሽ በማድረግ ተመራጭና ተወዳዳሪ የሆነ ሚዲያ ለመሆን እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ጉብኝቱ አስደሳች እንደነበር ያነሱት አቶ ካሳሁን፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ትምህርት በመውሰድና ተቋሙን ከህዝብ ጋር በማገናኘት በቅንጅት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review