የኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረበዓላት ለወንድማማችነት እና ለሀገራዊ አንድነት የማይተካ አስተዋጽኦ እንደላቸው የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ ፡፡
የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለ2018 የመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ምክርቤቱ በመልዕክቱም፣ በሀገራችን ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየው ብዝሃነት እና የህዝቦች አንድነት እንዲጸና፤ እያከናወነ የሚገኘውን የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ፣ የኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረበዓላት ለወንድማማችነት እና ለሀገራዊ አንድነት ያላቸውን የማይተካ አስተዋጽኦ እየገለጸ፣ ይህ እሴት ይበልጥ እንዲጎላ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በመልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና በመሳሰሉት ብዝሃነቶች የበለጸገች ጥንታዊት ሀገር ናት ያለው ምክር ቤቱ፣ የመስቀል በዓል ደግሞ የከተማችን እና የሀገራችን ልዩ ድምቀት ነው ብሏል፡፡
በዓሉ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው በዓላት አንዱ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የወል ሀብታችን ነው ሲልም ገልጿል።
የጋራ ምክርቤታችን ለመላዉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች፣ በዓሉ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የሰላም እንዲሆንላችሁ ያለውን መልካም ምኞት ይገልጿል ብሏል፡፡
በሀገራችን ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየው ብዝሃነት እና የህዝቦች አንድነት እንዲጸና፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያላት ቁመናዋ የላቀ እንዲሆን እያከናወነ የሚገኘውን የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያረጋግጣል ሲል ለኤ ኤም ኤን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በአፈወርቅ አለሙ