ኢሬቻ የኢትዮጵያዊያንን ማህበራዊ መስተጋብር የሚያደረጅ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing ኢሬቻ የኢትዮጵያዊያንን ማህበራዊ መስተጋብር የሚያደረጅ መሆኑ ተገለጸ

AMN- መስከረም 18/2018 ዓ.ም

በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው ኢሬቻ የክረምትን መዉጣትና የጸደይን መምጣት ተከትሎ የሁሉም ፍጥረታት ባለቤት የሆነው ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል ነዉ፡፡

በበዓሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው የሚሳተፍ ሲሆን፣ በአንድነት እና አብሮነት፣በፍቅር እና በመተሳሰብ የሚከበርም ነው፡፡

የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህበረት ዋና ጸሃፈ እና የቱለማ አባ ገዳ ጎበነ ሆላ፣ ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እና የምስጋና በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአንድነት እና አብሮነት በዓል የሆነው የኢሬቻ በዓል በንጹህ ልብ እና በይቅርታ ልቦና የሚከወን መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢሬቻ ኢትዮጵያዊያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የሚያስተሳስር በዓል መሆኑን የሚናገሩት አባ ገዳ ጎበነ ሆላ፣ በዓሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እና የአጎራባች ሀገራት ዜጎች የሚሳተፉበት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በመቻቸል፣ በመከባበር እና በመፈቃቀር በጋራ የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን የሚገልጹት አባ ገዳው፣ ይህ አብሮነት ከማህበራዊ መስተጋብር አልፎ በትዳር እና በደም የተሳሰረ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የአንድነት እና አብሮነት በዓል የሆነው ኢሬቻ ፣ በንጹህ ልብ እና በይቅርታ ልቦና የሚከወን መሆኑን አብራተዋል፡፡

በዚህ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሚታደሙበት በዓል ለመሳተፍ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ዜጎች በሰላም እንዲመጡ እና ከወገናቸው ጋር ጥሩ ጊዜን እንዲያሳልፉ መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የ2018 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል መስከረም 24 በአዲስ አበባ ሆረ ፊንፊኔ እንዲሁም መስከረም 25 ደግሞ በሆረ ሀርሰዲ ቢሾፍቱ የሚከበር መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review