ሕዳሴ ግድብ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል የቅኝ ግዛት ትርክትን በመቀየር በተፋሰሱ ሀገራት መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ መክፈቱን አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ ገለፁ

You are currently viewing ሕዳሴ ግድብ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል የቅኝ ግዛት ትርክትን በመቀየር በተፋሰሱ ሀገራት መካከል አዲስ የትብብር ምዕራፍ መክፈቱን አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ ገለፁ

AMN – መስከረም 18/2018 ዓ.ም

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል የቅኝ ግዛት ትርክትን ታሪክ በማድረግ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል የውሃ ሀብት ትብብር አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ ገለጹ።

80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒውዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ በተመድ የግብጽ ተወካይ በጠቅላላ ጉባዔው ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር ላይ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ላቀረቡት የሐሰት ክስ ምላሽ ሰጥታለች።

በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ በጠቅላላ ጉባኤው የስነ ስርዓት ደንብ ላይ የተቀመጠውን ምላሽ የመስጠት መብት (First Right of Reply) ተጠቅመው ግብጽ ላነሳችው ሀሳብ መልስ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ዮሴፍ ኢትዮጵያ የሰጠችው ምላሽ እውነታ ላይ የተመሰረተና የግብጽ ተደጋጋሚ ትርክቶች ሐሰተኛ መሆናቸውን በግልጽ ያሳየ መሆኑን ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የናይል ወንዝ የተፋሰሱን ሀገራት ለዘመናት ያቆራኘ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ለረጅም ጊዜ ትብብር ያማከለ አካሄድን ስትከተል መቆየቷን ጠቁመው፤ በተቃራኒው ግብፅ የሁለትዮሽ የቅኝ ግዛት ስምምነትን ለማስቀጠል በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ተገቢነት የሌለው ጫና እያሳደረች መሆኑን አመልክተዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የግብጽን የቅኝ ግዛት ትርክትና እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል አባዜ ፈጽሞ አትቀበለውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት ባደረገና ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የውሃ ሀብቷን እየተጠቀመች መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ መሻት የዜጎቿን ሕይወት መቀየር፣ መልማትና ማደግ እንዲሁም ዜጎች፣ ሆስፒታሎች እና ፋብሪካዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ዮሴፍ ኢትዮጵያ በትብብር መንፈስ እና በጋራ የመልማት መርህ ግብጽን ጨምሮ ከየትኛውም የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review