የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለጉብኝት ክፍት መደረግ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ በማነቃቃት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የቱሪዝም ዘርፍ ምሁራን ገልፀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።
የቱሪዝም ከፍተኛ ተመራማሪ እና ጸሐፊ መምህር አያሌው ሲሳይ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቱሪዝም እድገቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በግድቡ አማካኝነት የተፈጠረው ንጋት ሐይቅና ደሴቶች የተለያዩ ሁነቶችን ለማካሄድ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥሩ መሆናቸውንና በቱሪስቶች ዘንድ የኢትዮጵያን ተመራጭነት ያሳድገዋል ብለዋል።
በተለይም የውሃ ላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለማካሄድ፣ በጀልባዎች ለመዝናናት፣ አሳ ለማጥመድ፣ በደሴቶች ላይ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ለመክፈት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።
ግድቡ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉ የአካባቢው ማህበረሰብ፤ የቱሪዝም ዘርፉ ተዋናዮች ልዩ ልዩ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለቱሪስቶች በማቅረብ ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና ሆቴል ስራ አመራር ተመራማሪው ካሰኝ ብርሃኑ(ዶ/ር) ግድቡ ኢትዮጵያ የቱሪስቶችን ቀልብ የምትስብ ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ተጨማሪ የመስህብ ስፍራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአካባቢው ያሉ የቱሪዝም ጸጋዎችን በቀላሉ ለማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥርና ለስራ እድል ፈጠራም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ግድቡን ለመጎብኘት በሚሄዱ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የባህል ልውውጥ፣ አብሮነትና አንድነት ማጎልበት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከቱሪዝም የሚገኘውን ሀብት በሌሎች አካባቢዎች የሚካሄዱ ልማቶችን ለማፋጠን ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
ካሰኝ ብርሃኑ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከግድቡ የሚገኘውን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማሟላትና አገልግሎትን ማዘመን ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እንደተናገሩት፥ መንግስት በሕዳሴ ግድብ ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለማልማትና ለማስተዋወቅ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን በጀመረው የጉብኝት መርሃ ግብር የተለያዩ ጎብኚዎች ሕዳሴ ግድብን መጎብኘት መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።
ግድቡ የፈጠረውን የቱሪዝም ስፍራ ከሌሎች በአካባቢው ከሚገኙ የቱሪዝም መስህቦች ጋር በማቀናጀት የማስተዋወቅ ስራ እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ ስለሺ ገልጸዋል።