የዘንድሮዉ የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በአል መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም በርካታ የሃገር ዉስጥና የዉጭ ሃገር ታዳሚዎች በተገኙበት ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ ሁኔታ ይከበራል፡፡
በአሉ ሃገራዊ ማንሰራራትን እዉን ባደረገ መልኩ የሚከበር ሲሆን የምስጋና መርሃ ግብሩ የሚከናወንበት ሆረ ፊንፊኔ ለበዓል ምቹ መደረጉን አባገዳዎች ተናግረዋል፡፡
የገዳ ስርዓት ሁሉን አቃፊ ነው ያሉት ሃዩ ሆርዶፋ ደምሴ የፊንፊኔ አባገዳዎች አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ናቸው ።

አሁን ላይ አዲስ አበባ አምራና ተውባ እንዲሁም የአፍሪካ ተምሳሌት ሆና በምትገኝበት በዚህ ሰዓት፤ የኢሬቻ በዓልን በደስታ እና በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ይህም ልዩ የደስታ ስሜት አለው ነው ያሉት ።
ለኢሬቻ በዓል በጤና ሰላደረስከን እናመሰግንሃለን፤ የዘራነው አፍርቶ ለመብላት እና ለመጠጣት አብቃን ብሎ የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪውን የሚለንምንበት፣ የሚማጸንበት እና ከፈጣሪ ጋር የሚገናኝበት መሆኑን ሃዩ ሆርዶፋ ደምሴ አብራርተዋል።
ታዲያ ይህንን በዓል ለማክበር የሆረ ፊንፊኔ ማክበሪያ ቦታ ለበዓሉ ዝግጁ መሆኑን ነው ሃዩ ሆርዶፋ የተናገሩት ።
አባ ገዳ ሀዩ ዘውዱ መብራ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማክበሪያ ቦታዎችን ከማልማት እና ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ረገድ የተሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
በመሆኑም የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ማክበርያ ቦታም በዚሁ ልክ ለምቶ ዝግጁ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

ኦዳ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ጥላ፣ የአባቶች መመረቂያ ፣ የሽምግልናና የእርቅ ቦታ ነው ያሉት አባገዳ ሀዩ ዘውዱ ከአመታት በፊት በቦታው ተክለውት የነበረው ዋርካ (ኦዳ) አድጎ በማየታቸው መደሰታቸዉን ይናገራሉ።
አዲስ አበባ በሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ እየተዘጋጀች እንደምትገኝ እና ጥሩ ጊዜም እንደሚያሳልፉ ተስፋቸዉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በአብሮነት፣በአንድነትና በቁጭት ሃገሪቱን በማልማት ዕድገቷን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉም ነው አባገዳዎቹ የተናገሩት፡፡
የዘንድሮዉ የሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል መስከረም 24/2018 ዓ.ም እንዲሁም የሆረ ሃርሰዲ የኢሬቻ በዓል መስከረም 25/2018 ዓ.ም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በተገኙበት በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ተከብሮ ይዉላል፡፡
በዓሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል፡፡
በፍሬህይወት ብርሃኑ