ኢትዮጵያ እና ጣሊያን በተለያዩ የልማት መስኮች ያላቸው አጋርነትና ትብብር እያደገ መምጣቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሽሬ እና ጎንደር ሆስፒታሎችን ለማጠናከር የሚያስችል የ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት በኢትዮጵያ ከጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ ጋር በተፈራረሙበት ወቅት ነው።
የድጋፍ ስምምነቱ የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን አጋርነት ከፍ ለማድረግ ትልቅ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት፤ የተደረገው ድጋፍ ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በሆስፒታሎቹ ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የረጅም ዓመታት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው በመጥቀስ፥ በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ በትምህርትና በባህል ዘርፎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የዛሬው ስምምነትም ሁለቱ ሀገራት በሁሉም ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይና ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማስፋት የጀመረችውን ሥራ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል ያለው ትብብርና አጋርነት በዘላቂነት እና በጋራ ብልጽግና ላይ ተመስርቶ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት ያላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዛሬው የድጋፍ ስምምነትም በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን የሚያጠናክርና የሀገራቱን ትብብር የሚያሳድግ መሆኑን አንስተዋል።
ጣሊያን ከዚህ ቀደም በበርካታ ዘርፎች የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ መቆየቷን መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።