በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሰዎች የሚታደሞባቸው የአደባባይ በዓላት ከሀገሬው ሰው አልፈው የውጭ ዜጎችን በመሳብ ወደ አለም አቀፍነት እየተሻገሩ ይገኛሉ።
ባህል ፣ ሀይማኖት እና ታሪካዊ መነሻ ያላቸው እነዚህ በዓላት በየአመቱ የሚሳተፍባቸው የህዝብ ቁጥር ከመጨመሩ ባለፈ ሀገራዊ መገለጫም እየሆኑ እንደሚገኙ ይነገራል። በኢትዮጵያ የመስቀል ደመራ ፣ ጥምቀት እና የኢሬቻ የአደባባይ በዓላት ባህላዊ እና ሀይማኖታዊ መገለጫን ተላብሰው በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በመላው ሀገሪቱ በድምቀት የተከበር ሲሆን የኢሬቻ እና ጥምቀት በዓላት ደግሞ በቀጣይ ይጠበቃሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው በርካታ የአደባባይ ፌስቲቫሎችን ስንመለከት የብራዚሉን የሪዮ ካርኒቫል ቀዳሚ ሆኖ እናገኘዋለን ።
የአለማችን ታላቁ ፌስቲቫል የሚታወቀው ይህ ክብረ በዓል ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ባህልን በሰፊው በመላበስ በደማቅ ቀለሞች ባሸበረቁ አልባሳት ታጅቦ በጭፈራ ፥ በሙዚቃ እና በተለያዩ ትርዒቶች የሚከወንበት ነው። የግሎባል ዎርክ ኤንድ ትራቭል መረጃ እንደሚጠቁመው ለቀናት በሚቆየው በዚህ ፌስቲቫል ላይ በቀን እስከ 2ሚሊየን ሰው ይታደማል።
በጥቅምት የመጀመሪያው ሳምንት እሁድ በጀርመን የሚከበረው ኦክቶበርፌስት አለም አቀፍ ዝናን ካገኙ በርካታ ሰዎች ከሚሳተፉባቸው ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ነው። የምርት መሰብሰቢያ ወቅት መጠናቀቁን ተከትሎ የሚከበረው ይህ ፌስቲቫል በ1810 ከነበረ ንጉሳዊ ሰርግ ጋር በማያያዝ የሚከበር ሽህ አመታትን ያስቆጠረ ክብረ በዓል ነው።
የባቫሪያን ባህል ማስቀጠል የሚል አላማ ያለው ሲሆን ክፍለ ዘመን ያስቆጠሩ ታሪኮች እና አፈ ታሪኮች ይዘከሩበታል፤ ሙዚቃ አልባሳት እና ጀርመኖች የሚታወቁበት ቢራ የበዓሉ ማድመቂያዎች ናቸው። ጥቅምት እና ህዳር ላይ የሚከበረው ዲዋሊ የተሰኘው ክበረ በዓል በህንድ ከሚከበሩ በርካታ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ፌስቲቫሎች መካከል ተጠቃሽ ነው። የብርሀን ፌስቲቫል በመባል የሚታወቀው ክብረ በዓል ብርሀን ጨለማን ያሸነፈበት ወይም ጥሩ መጥፎን የረታበት ነው በሚል ይከበራል።
በዕለቱ ህንዳዊያን በቀለም ያሸበረቁ አልባሳትን በመልበስ በመኖሪያ ቤቶች እና በህንጻዎች ላይ ፋኖሶችን በመስቀል እና ጣፋጭ ምግቦችን ስጦታ በመቀያየር ያከብሩታል። የቻይና አዲስ አመት ፣ የኒውኦርሊያንስ የጃዝ ሙዚቃ ፌስቲቫል (ማርዲ ግራስ) እና የስፔኑ ላ ቶማቲና አለም አቀፍ ዝናን ካገኙ በርካታ ህዝብ ከሚታደምባቸው በአላት መካከል ይጠቀሳሉ።
የኦሮሞ ህዝብ ከጭጋግ ወራት ወደ ብራ ላሸጋገረው ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት የኢሬቻ በዓል በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ በድምቀት ይከበራል።
በዳዊት በሪሁን