ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ ገልፀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 80ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከመስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባዔው ግብፅ የናይል ወንዝ የብቸኛ ባለቤትነት የሚመስሉ የተለመዱ አቤቱታዎችንና ክሶችን በተወካይዋ አማካኝነት አንስታለች፡፡
በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ የገለፁት አምባሳደር ዮሴፍ፤ በአንፃሩ ግብፅ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ተገቢነት የሌለው ጫና እያሳደረች እንደምትገኝ አመላክተዋል፡፡
የናይል ወንዝ የተፋሰሱን ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ያቆራኘ የተፈጥሮ ሀብት መሆኑን አምባሳደር ዮሴፍ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህንን ትስስር ለማጠናከር ስትሰራ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡
ግብፅ በቅርቡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በፃፈችው መሠረተ ቢስ የክስ ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ ተገቢውን ምላሽ መስጠቷን ገልፀዋል ፡፡
ምላሹ እውነታ ላይ የተመሰረተና የግብፅ ተደጋጋሚ ትርክቶችን ሀሰተኛ መሆናቸውን በግልፅ ያሳየ መሆኑን አምባሳደሩ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ አጠቃቀም ላይ ለረዥም ጊዜ ትብብርን ያማከለ አካሄድን ስትከተል መቆየቷን የገለፁት አምባሳደሩ፤ በተቃራኒው ግብፅ ታሪካዊ መብት አለኝ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ጊዜው ያለፈበት የቀኝ ግዛት እሳቤ እያራመደች እንደምትገኝም አብራርተዋል ፡፡
ኢትዮጵያ የግብፅን የቀኝ ግዛት ትርክት እና እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል አባዜን ፈጽሞ አትቀበለውም ሲሉም አምባሳደሩ ለጉባዔው የሃገራቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በተፈራረመችው የመርሆች ስምምነት መሰረት የግድቡን ሙሌትና ሥራ አስመልክቶ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ግልፅነት በተሞላበት ሁኔታ መረጃ ተደራሽ ስታደርግ መቆየቷንም አብራርተዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁን የገለፁት አምባሳደሩ፤ ይህም ለኢትዮጵያ፣ ለናይል ተፋሰስ ሀገራትና በአፍሪካ ልማት እና ብልፅግናን ለሚሹ ሁሉ ትልቅ እርካታ የሰጠ እንደሆነ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ ታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡
በጉባዔው ላይ በሠላም፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዘላቂ ልማት፣ በድጂታል አካታችነት፣ በሰብዓዊነት እና በኢኮኖሚ አጠቃቀም ዙሪያ እና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይትና ምክክር እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በ-በረከት ጌታቸው