በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ

You are currently viewing በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታወቀ

AMN መስከረም 20/2018

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ሀገራዊ ምክክር በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ምክንያት የሆኑትን ጉዳዮች በጥናትና በህዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ ሀገራዊ ምክክር በማካሄድና ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ ለተግባራዊነቱ የመከታተያ ሥርዓት በመዘርጋት ለብሔራዊ መግባባት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ እንዳሉት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ በማቅረብ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በማካሄድ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር አጀንዳ የማሰባሰብ ምክክር በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት በውጭ ከሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በገጽ ለገጽና በበይነ-መረብ፤ በሀገር ውስጥ ከሚኖሩት ጋር ደግሞ በገጽ ለገጽ ገንቢ ምክክር ማካሄድ ተችሏል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በሌሎች ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ አጀንዳቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚፈጠር ገልጸው፤ ከወዲሁ አጀንዳቸውን እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገራዊ ምክክሩ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደትም በውጭ የዳያስፖራ ማህበሰረብ አባላት ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በአጀንዳነት እያቀረቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የፖለቲካ ዓላማቸውን በትጥቅ ለማሳካት በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላትም በሀገራዊ ምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ፤ በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉበት እድል ተፈጥሯል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዳያስፖራ አደረጃጀቶችና በቀጥታ አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review