ለኪነ ጥበብ ዘርፍ ትኩረት መሰጠቱ በሙያው ያሉ ስዎች ስራቸውን በብቃትና በጥራት ለመስራት ከማስቻሉ ባለፈ ወጣቶችም በተነሳሽነት ወደ ሙያው እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርግ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይህን ያሉት የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ኮምፕሌክ በተመረቀበት ወቅት ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው፡፡
አርቲስት ሺመልስ ለጋስ በአራቱም ቴአትር ቤቶች እንደሰራና ጡረታ ከወጣ በኋላ እንደገና ተመልሶ ወደ ቀደመ ሙያው መቀላቀሉን ይገልፃል፡፡

አርቲስቱ ሰሞኑን የተመረቀው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ኮምፕሌክስ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል እንደነበር አስታውሶ፣ እንዲህ አምሮና ዘመናዊነቱን ተላብሶ ለምረቃ በመብቃቱ የተሰማውን ደስታ በአንደናቆት ገልጿል፡፡
ሌላኛው የኪነ ጥበብ ሰው አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ በበኩሉ፣ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ኮምፕሌክስ ለህጻናት ልጆች ታስቦ ደረጃውን በጠበቀና ዘመናዊነትን ተላብሶ በአማረና ወቅቱን በዋጀ መንገድ መሰራቱ እጅግ አስደስቶኛል ብሏል፡፡
ሀገራት የተሰሩት በትርክት ነው፤ ችግር ሲያጋጥማቸውም ከችግራቸው የሚወጡት በትርክት ነው፤ ይህ ትርክት ደግሞ የሚገለጸው በኪነ ጥበብ ነው ያለው ደግሞ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው እና የኪነ ጥበብ ባለሙያው ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ነው፡፡

ስለ ሀገር የሚሰሩ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስራዎችን ወደ ህዝብ ለማስረጽ ህዝባዊ ስፍራዎችን ማብዛት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁሟል፡፡
አዲስ አበባ አራት የቴአትር ቤቶች ቢኖሯትም፣ ሰሞኑን ተጠናቆ ለምርቃት የበቃው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ማዕከል ግን እጅግ ዘመናዊና ዘመኑን የዋጀ እንደሆነም ተናግሯል፡፡
ሌላኛው የኪነ ጥበብ ሰው አርቲስት ዳዊት ይፍሩ በበኩሉ፤ እስካሁን ባለፍንባቸው ጊዜያት የነበሩ የኪነ ጥበብ ማሳያ መድረኮችም ሆኑ ሌሎች ስፍራዎች ብዙ ትኩረት የተሰጣቸውና ግብዓቶችም በአግባቡ የተሟሉ እንዳልነበሩ ይገልፃል፡፡
ሰሞኑን የተመረቀው የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር እና ሲኒማ ኮምፕሌክስ ግን ለኪነ ጥበቡ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ያለው አርቲስቱ፤ ስራዎችን በብቃትና በጥራት ለመስራት ከማስቻሉም በላይ ወጣቶች ወደ ኪነጥበቡ ዘርፍ በተነሳሽነት እንዲቀላቀሉ ያስችላል ብሏል፡፡
በአስማረ መኮንን