ለፍፃሜ የሚጠበቁት ባርሰሎና እና ፓሪሰን ዠርማ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ

You are currently viewing ለፍፃሜ የሚጠበቁት ባርሰሎና እና ፓሪሰን ዠርማ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ

AMN-መስከረም 21/2018 ዓ.ም

ባለፈው ዓመት የተካሄደውን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በርካቶች ፓሪሰን ዠርማ እና ባርሰሎና እንዲፋለሙበት ተመኝተው ነበር።

በግማሽ ፍፃሜው ኢንተር ሚላን ባርሰሎናን በድምር ውጤት 7ለ6 ማሸነፉ የሁለቱን አስደናቂ ቡድኖች የፍፃሜ ፍልሚያ መመልከት አልተቻለም። ሁለቱ ክለቦች እንከን የለሽ በሚመስለው የማጥቃት አጨዋወታቸው የገለልተኛ ደጋፊ ተመራጭ ሆነዋል። ባርሰሎና ባለፈው ዓመት ምንም እንኳን ለፍፃሜ ባይበቃም 43 ግብ በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን ነበር።

ሻምፒዮኑ ፓሪሰን ዠርማም 38 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። በዘንድሮ ውድድር በሊግ ፎርማት የሁለተኛ የጨዋታ ቀን ላይ የተገናኙት ክለቦቹ አስደናቂ ፉክክር ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጨዋታው ላሚን ያማል የተመለሰለት ባርሰሎና ግብ ጠባቂው ጆሀን ጋርሺያ ፣ ራፊንሃ እና ጋቪን በጉዳት አይጠቀምም። በፓሪሰን ዠርማ በኩልም የባሎን ድ ኦር አሸናፊው ኡስማን ዴምቤሌን ጨምሮ አምበሉ ማርኪንሆስ ፣ ኪቪችሃ ክቫራስኬሊያ እና ዴዚሪ ዱዌ ጉዳት ከጨዋታው ውጪ አድርጓቸዋል።

ጉዳት ቢበዛም በሁለቱም ቡድን ስብስብ ውስጥ ያሉ ቀሪ ተጫዋቾች የስፖርት ቤተሰቡ የሚጠብቀውን ድንቅ ፉክክር ለማሳየት ብቁ ናቸው። ፓሪሰን ዠርማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ ባለድል ያደረገው ሊውስ ኤነሪኬ በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት የገዘፈ ታሪክ ወደ ሰራበት ባርሰሎና ያቀናል።

በዘንድሮ ቻምፒየንስ ሊግ ባርሰሎና ኒውካስትል ዩናይትድን ፣ ፓሪሰን ዠርማ ደግሞ አታላንታን በመርታት አጀማመራቸውን አሳምረዋል። ባርሰሎና እና ፓሪሰን ዠርመ ከዚህ ቀደም ለ15 ጊዜ ተገናኝተው ባርሰሎና ስድስት ጊዜ ድል በማድረግ የበላይነቱን ይወስዳል።

ፓሪሰን ዠርመ በአንፃሩ አምስት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። በኤስታዲዮ ኦሎምፒኮ ሊውስ ካምፓኒ ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ እንግሊዛዊው ዋና ዳኛ ማይክል ኦሊቨር ይመሩታል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review