በአፍሪካ የትምህርትና ስልጠና ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሳደግ ሀገራት ትብብራቸውን የበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመምህራን ትምህርት ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
“በአፍሪካ የመምህራን ትምህርት ስርዓትን መቀየር” በሚል መሪ ሀሳብ በተጀመረው ኮንፍረንስ የህብረቱ አባል ሀገራት የትምህርት ሚኒስትሮች፣ የመምህራን ማህበራት ተወካዮች፣ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና የልማት አጋሮች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ ትምህርት ለሰው ሃብት ልማትና ለምጣኔ ሀብት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።
በአፍሪካ የሚፈለገውን ልማትና ዕድገት ለማምጣት የትምህርት ተደራሽነት ላይ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራትና የመምህራን እጥረት ላይ እንደ አህጉር አሁንም ያልተፈታ ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አባል ሀገራቱ ትብብራቸውን የበለጠ ማጠናከር አለባቸው ብለዋል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የትምህርት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ሞሃመድ ቤልሆሲን በበኩላቸው፣ በአፍሪካ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትና ሳይንስና ፈጠራን የበለጠ ለማዳበር የመምህራንን አቅም ማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለዚህም ለመምህራን አቅም ግንባታ የተለያዩ ኤኒሼቲቮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ የ2063 የልማት ዕቅዶች ዕውቀት መር በሆነ መንገድ ቢተገበሩ ውጤታማ ይሆናሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡