በኖርዲክ አገሮች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ እና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ የዲያስፖራ ተወካዮችን ለማስመረጥ ወደ ስዊድን የተጓዘው የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኮሚሽነሮች ልዑካን ቡድን በስዊድን የተለያዩ ከተሞች ከሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እና የኃይማኖት አባቶች ጋር ተወያይቷል፡፡
ልዑካን ቡድኑ ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና የቀጣይ አቅጣጫዎቹን በተመለከተ ለአደረጃጀቶቹ ገለፃ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
በመጪው ቅዳሜ መስከረም 24/2018 ዓ.ም በስዊድንና በአካባቢው አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አጀንዳ ለማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን ለመለየት የውይይት መድረክ እንደሚያካሂድ ለአደረጃጀቶቹ ማስገንዘቡንም አስታውቋል፡፡
የዲያስፖራ አደረጃጀት አመራሮች በቀጣይ ቅዳሜ የሚደረገውን የውይይት ሂደት አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ኮሚሽነሮች በተነሱ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸውም ተገልጿል።
መድረኩ ሀገራዊ ፋይዳቸው የላቀ አጀንዳዎች የሚሰበሰቡበትና የተሳካ እንዲሆን፤ በአካባቢው የሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ኮሚሽኑን እንዲያግዙ መጠየቁም በተላከው መረጃ ተገልጿል።
አደረጃጀቶቹ እራሳቸው በምክክር መድረኩ በንቃት እንዲሳተፉና በስካንዲኔቪያ የሚገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንዲሳተፉ በማስተባበርና በቅስቀሳ እንዲያግዙ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ በስዊድንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ የሚያሰባስብበት እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች የሚለይበት የምክክር መድረክ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 24/2018 ወይም ኦክቶበር 4/2025 ከጠዋቱ 9፡00 AM ጀምሮ በስቶክሆልም የሚካሄድ እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል።