ሃደ ሲንቄ – የኦሮሞ ህዝብ ለሴቶች ያለውን ክብር የሚገልፅበት ትልቁ ባህላዊ እሴት ነዉ

You are currently viewing ሃደ ሲንቄ – የኦሮሞ ህዝብ ለሴቶች ያለውን ክብር የሚገልፅበት ትልቁ ባህላዊ እሴት ነዉ

AMN – መስከረም 21/2018 ዓ.ም

የኢሬቻ በዓል የመከባበር እሴት ፤ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚታይበት እና ከአስቸጋሪዉና ከጨለማዉ የክረምት ወቅት ወደ ብራ ወይም ወደ ብርሃን ላሸጋገረዉ አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበት፣ ፍቅር እና ዕርቅ የሚንጸባረቅበት ትልቅ በዓል ነው።

በገዳ ስርዓት ዉስጥ ቅልቅ ከበሬታ ከሚሰጣቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶችና እናቶች ቀዳሚዎቹ ናቸዉ፡፡ የቱለማ አባገዳ ፍቃዱ አበራ የኦሮሞ ህዝብ ለሴቶች ያለውን ክብር በአደባባይ የሚገልፅበት ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል መሆኑን ይገልጻሉ።

በኢሬቻ የአከባበር ሥርዓት ላይ ሀደ ሲንቄዎች ጉልህ ሚና እንዳላቸዉ የገለፁት አባገዳ ፍቃዱ፤ በበአል ዝግጅት የሀደ ሲንቄዎች ሚና የሚጀምረው ከቤት ነው፤ ይህም ለበዓሉ የሚሆኑ ባሕላዊ ምግቦችን፣ አልባሳት እና የበዓሉ ማድመቂያ ጌጣጌጦችን በማዘጋጀት እና በመዋብ ነው ይላሉ፡፡ በኢሬቻ የአከባበር ሥርዓት ላይም በቅድሚያ ልጃገረዶች ከፊት የሚመሩ ሲሆን፤ በመቀጠል ሀደ ሲንቄዎች ተከትለው ይጓዛሉ፤ ቀጥሎም አባገዳዎች እና ፎሌዎች በረድፍ ይከተላሉ።

ይህም በኢሬቻ እሴት መሰረት ሂደቱ የትውልድን ቀጣይነት እና ቅብብሎሽ እንዲሁም የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ለማሳየት የሚከናወን ነው ይላሉ አባገዳ ፍቃዱ ። በገዳ ስርዓት ውስጥ እናቶች አስታራቂ በመሆናቸው ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣቸው የገለፁት አባገዳ ፍቃዱ፤ ለዚህም ምሳሌነት የእርቅ በዓል በሆነው የኢሬቻ ሰላም በማውረድ በኩል ቀዳሚ የሆኑት ሴቶች ከፊት እንደሚመሩ ገልፀዋል፡፡

በዚህም በበዓሉ ቀን አከባቢያቸውን በሚገልጽ ባህላዊ አልባሳት ደምቀውና ፈክተው ሲንቄ፣ ኦኮሌ እና ጫጩ በመያዝ የምስጋና እና የተማጽኖ ዜማዎችን እያዜሙ በአሉ ወደ የሚከበርበት ቦታ ከፊት እየመሩ ይጓዛሉ።

የገዳ ስርዓት አንዱ አካል እና ነጸብራቅ የሆነው ኢሬቻ በዓል፤ የፍቅር፣ የሰላም እና እርቅ በዓል በመሆኑ በእለቱ ሀደ ሲንቄዎች መሬሆ’ ዞሮ መጣ፤ ‘አራሮ’ እባክህ ታረቀን እያሉ ለፈጣሪ ምስጋናና ምልጃ እንደሚያቀርቡ አስረድተዋል።

የኢሬቻ ክብረ በዓል የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን የሚያሰባስብ እና ያለምንም ብሔር፣ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ልዩነት የሚከበር ሲሆን፤ በዓሉ ከሃገር ውስጥ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጎብኝዎች የሚታደሙት ክብረ በዓል ነው።

በፍሬህይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review