የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቁ

You are currently viewing የሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታወቁ

AMN – መስከረም 21/2018 ዓ.ም

በርካታ ህዝብ የሚታደምባቸው የሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላት በስኬት እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ ወጥቶ በታላቅ ድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል የኢሬቻ በዓል አንዱ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፣ በዓሉ በሠላም በሚከበርበት የፀጥታና ደህንነት አካላት አመራሮች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ሀይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ መከበሩን ያስታወሰው ፖሊስ፣ መስከረም 24 እና 25 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበሩት የሆረ ፊንፊኔ እና የሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓላትም ባህላዊ እሴታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ የፀጥታ አካላት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

በዓላቱን ህዝቡ በአብሮነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ የሚያከበራቸው በህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው የምስጋና በዓላት በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከልዩ ልዩ ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች፣ ከአጎራባች አገራት ጭምር የሚመጡ እንግዶችን የሚሳተፍባቸው በዓላት ስለሆኑ በዓላቱ በሠላም ተከብረው እንግዶች ወደ መጡበት በሠላም እንዲመለሱ የፀጥታ ተቋማት በቂ የሰው ኃይል በመመደብ እና የቅድመ ወንጀል መከለከልና የቁጥጥሩ ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረግ አኳያ ተገቢውን ዝግጅት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች በመቻቻል፣ በመከባበርና በመፈቃቀር የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን አስረድተው የአንድነት እና የአብሮነት በዓል የሆነው የኢሬቻ በዓል ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲከበር መደረጉ ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት ከማጎናፀፉም ባሻገር የህዝብ አብሮነት ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ የተከበሩ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓላት በስኬት መከበራቸው የጠቅላይ መምሪያው አዛዥ አስታውሰው የዘንደሮ የኢሬቻ በዓል በስኬት እንዲከበር የፀጥታና ደህንት ተቋማት ከበዓሉ አከባበር ኮሚቴዎች፣ ከኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት፣ ከሀደ ስንቄዎች፣ ከፎሌዎች ጋር በጥምረት እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የተለያዩ የሸገር ከተማ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማችን እንደሚገባ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የሀገራችን ክፍሎች የሆራ ሀርሰዴ በዓልን ለማክበር በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች ከተማችንን አቋርጠው የሚሄዱ ስለሆነ በዓሉን የሚመጥን የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

እንደሁልጊዜው ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ፤ ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖርና ከበዓሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ቁሳቁስ ይዞ ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑም ኮሚሽነር ጌቱ አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፣ የአብሮነት መገለጫ የሆነውን የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ “ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በክፍለ ከተማ ደረጃ እየተከበረ እንደሆነና ልዩ ልዩ አካላት በተገኙበት የሆራ ፊንፊኔ የሚከበርበት የኢሬቻ ፓርክ የማፅዳት ስራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተሰራውን የቅንጅት ስራ በማጠናከር የኢሬቻ በዓልም እሴቱን ጠብቆ በሠላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች የሠላም ሰራዊት አባላት በቂ ኦረንቴሽን ወስደው ወደ ስራ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘት በፌዴራል ፖሊስ የለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review