የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ምቹ፣ ፅዱና ውብ በሆነ ስፍራ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ተግባራ መከናወናቸው ተገለፀ

You are currently viewing የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ምቹ፣ ፅዱና ውብ በሆነ ስፍራ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ተግባራ መከናወናቸው ተገለፀ

AMN – መስከረም 22/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ምቹ፣ ፅዱና ውብ በሆነ ስፍራ ለማስተናገድ እንዲቻል የኢሬቻ ማክበሪያ ስፍራ የሆነውን ኢሬቻ ፓርክን የማፅዳት ስራ ተከናውኗል፡፡

የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላትና ከገዳ ስርዓት መገለጫ መካል አንዱ ነው፡፡ በዚህ የምስጋና በዓል ላይ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ የሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡

በበዓሉ የሚገኙ ተሳታዎች ምቹ፣ ፅዱና ውብ በሆነ ስፍራ በዓሉን እንዲያከብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

በዚህም የፊታችን መስከረም 24 የሚከበረውን ሆረ ፊንፊኔ በዓል ማክበሪያ ስፍራ የሆነውን የኢሬቻ ፓርክን የማጽዳት ስራ ተከናውኗል፡፡

በዚህ የፅዳት ንቅናቄ መርሃ ግብር ላይ የከተማዋ ከፍተኛ መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አርቲስቶች፣ የጽዳት አምባሳደሮች የመንገድ ጥርጊያ ባለሙያዎች እና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ እንደገለጹት፣ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በምቹ፣ በፅዱና ውብ በሆነ ስፍራ ለማስተናገድ የሚያስችሉ ተግባራ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዋና ስራ አስኪያጁ አያይዘውም፣ ይህ አብሮነታችን የሚፀባረቅበት በዓል ኢትዮጵያዊያን በአብሮነት እውን በአደረጉት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚም ምስክር ነጋሽ ዶ/ር፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ በዓል የሚከበርባት ስፍራ መሆኗ እድለኛ ያስብላታል ያሉ ሲሆን፣ በእለቱ የሚመጣውን የበዓሉ ተሳታፊ በደስታ ለመቀበል እና ለመሸኘት አስፈላጊውን ዝግጅት እንደተደረገ ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገዘኸኝ ዴሲሳ በበኩላቸው፣ የአደባባይ እና ህዝባዊ በዓሎች ከመከበራቸው በፊት እና ከተከበሩ ማግስት አካባቢዎችን ፅዱና ውብ የማድረጉ ተግባር ለተሳታፊዎች ክብር የሚሰጥ፣ በዓሉን በድምቀት እንዲያከብሩ ከማስቻል ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review