በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን ተወዳዳሪነት በማሳደግ የዲፕሎማቲክ ማዕከልነቷን በተግባር የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ አፍሪካ ህብረትና በኢትዮጵያ የቺሊ አምባሳደር ሮድሪጎ ጉዝማን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ አፍሪካ ህብረትና ኢትዮጵያ የቺሊ አምባሳደር ሮድሪጎ ጉዝማን እንዳሉት፤ ቺሊንና ኢትዮጵያን በርካታ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ።
ሁለቱም አገራት በአካባቢ ጥበቃ ላይ ጠንካራ አቋም ያላቸው መሆናቸውን አንስተው፤ ቺሊ በደቡብ ለደቡብ ትብብር ከአፍሪካ አገራት ጋር ትስስር ያላት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፤ አፍሪካ ብዝሃ ሀብት ያላት አህጉር በመሆኗ ብዝሃ ዘርፍ ትብብራችንን ለማጠናከር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
አምባሳደሩ ግጥምና ሙዚቃን በመሳሰሉ የኪነ ጥበብ ስራዎች የሁለቱን አገራት የባህል ትስስር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናና የዲፕሎማቲክ ማዕከል በመሆኗ በከተማዋ የተደረገው ለውጥ ውበትና ዘመናዊነትን ያላበሳት መሆኑንም ገልፀዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ መዲናዋን ዘመናዊና ምቹ በማድረግ ተወዳዳሪነቷን የሚያሳድግ መሆኑንም ነው የተናገሩት።