በመደመር መንግሥት መፅሐፍ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት መድረክ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተካሄዷል፡፡
መጽሃፉ ከፋፋይና አጨቃጫቂ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት አቻችሎና አዳምሮ በዜጎች መካከል የእርስ በርስ መከባበር፣ ማህበራዊ መረዳዳት እንዲኖር ሀሳብ የሚለግስ ስለመሆኑም ተነግሯል።
ቀደም ሲል መደመር፣ የመደመር መንገድና የመደመር ትውልድ የተሰኙ መፃህፍትን ለንባብ ያበቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ ደግሞ የመደመር መንግሥት የተሰኘ መፅሐፍ አስመርቀው ለንባብ ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡
መፅሐፉ በውስጡ በያዛቸው ፍሬ ሐሳቦች ላይ ያተኮሩ የተለያዩ መድረኮችም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በቂርቆስ ክፍለ ከተማም ሙሁራን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) ፣ የመድረኩ ዋነኛ ዓላማ የመደመር መንግሥት መፀሐፍ የወደፊት ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ለማሻገር ለያዝነው ጉዞ እንደ ፍኖተ ካርታ እንደመስፈንጠሪያ የሚያገለግለን ነው ባይ ናቸው። ስለዚህ በዝርዝር አውቀን የስራ መመሪያ ልናደርገው እንደሚገባም ነው ብለዋል፡፡

የመደመር መንግሠሥት መፅሃፍ ትውልዶችን ከፋፍሎ እንደየ ድርሻቸው ሃላፊነትን የሰጠ መሆኑን ያነሱት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ የመደመር መንግስት መፅሓፍ ደግሞ መንግስቱ በምን አይነት አስተሳሰብ ይመራ ተቋማት እንዴት ይደራጁ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰናስል ተደማምረው ሀገርን እንዴት ማበልፀግ እንደሚቻል የሚያሳይ መፅሀፍ ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህርና ተመራመሪ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ የመወያያ ሃሳብ በአቀረቡበት ሰዓት መፅሐፉ ያለንበትን ሁኔታ ከቦታ ከጊዜና ከማህበረሰብ አኳያ ለይተን እንድናውቅ ያስቻለ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። ከፋፋይና አጨቃጫቂ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት አቻችሎና አዳምሮ በዜጎች መካከል የእርስ በርስ መከባበር ማህበራዊ መረዳዳት እንዲኖር ሀሳብ የሚለግስ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) አያይዘውም፣ መፅሀፉ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች በተፃራሪ ነገሮች የተወጠሩ ናቸው፤ ብሎ ከማሰብ ይልቅ የሚያያዙበትን እና አብሮ የሚሄዱበትን ሁኔታዎች የሚያሳይ ለአብሮነትን አስቻይ ሁኔታዎችን የሚጠቁም ነው ብለዋል፡፡
መጽሃፉ የተቃርኖ ትርክትን በማንሳት መውጫ መፍትሄዎችን የሚጠቁም የስሜት ብሰለትን እንዲኖረን የሚያስገነዝብ ነው ያሌት ደግሞ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ የውጪ ቋንቋ ጥናት ተመራማሪ ዮሴፍ ቤካ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
በውይይቱ ላይ የታደሙት ተሳታፊዎችም መፅሃፉ እንደሀገር ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን የሚዳስስ እንዲሁም የመውጫ መፍትሄ መንገዶችን የሚጠቁም እና አማራጭ ሀሳቦችን የሚያስተናግድ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡
በታምሩ ደምሴ