ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ልማት በሰጠችው ትኩረት የሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረቷን እየገነባች መሆኑን አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ልማት በሰጠችው ትኩረት የሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረቷን እየገነባች መሆኑን አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ

AMN መስከረም 22/2018

ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ ልማት በሰጠችው ትኩረት የሁለንተናዊ ብልፅግና መሰረት እየገነባች መሆኑን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም ባንክ በጋራ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ፎረም 2025 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ለኢትዮጵያ ይህ ጉባኤ ወቅታዊ እና አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የሀገርን ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና ለማስቀጠል የሰብዓዊ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በትምህርት፣ በጤና፣ በሥነ-ምግብና ክህሎትን ማዳበር የሀገራዊ የለውጥ መሠረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ዘመኑን የዋጀ ብቁ፣ ጤናማና ተወዳዳሪ ትውልድ መገንባት የሚያስችሉ የሰብዓዊ ልማት ሥራዎችን በስኬታማነት እየተገበረች ትገኛለች ነው ያሉት።

በትምህርት፣ በጤና፣ በሥርዓተ ምግብና በማህበራዊ ጥበቃ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገቡና ለሁለንተናዊ ብልፅግና ጠንካራ መሰረት እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ጥራት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትና ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

የሙያና ክህሎት ተቋማትም በርካታ ተማሪዎችን እያስተናገዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ የትምህርት ዘርፍ የሰብዓዊ ልማት ሥራ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ብቁ ትውልድ የማዘጋጀት ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑንም ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍም ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ለማዳረስ ውጤታማ የጤና ኤክስቴንሽንን በመተግበር ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ስኬት አስመዝግበናል ነው ያሉት።

መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን በማዳረስ የእናቶችና ህጻናት ሞትን መቀነስ ተችሏል ያሉት አፈ ጉባኤው፥ በርካታ ሚሊዮን ቤተሰቦች የተሟላ የህክምና አገልግሎት እያገኙ ናቸው ብለዋል።

የተመጣጠነ ስርዓተ ምግብን በማጠናከር በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ የመገንባት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አፈ ጉባኤው አክለውም ሰብዓዊ ልማት የኢኮኖሚ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉም ህጻናት፣ ወጣቶችና ሴቶች በእያንዳንዱ የልማት ማዕቀፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ለሀገርና ለዓለም ብቁ ትውልድ የመገንባት የጋራ ግብ እንደሆነም አስረድተዋል።

በመሆኑም አፍሪካውያን ለሰብዓዊ ልማት ትኩረት በመስጠት አህጉራዊ አቅምን በአግባቡ ለመጠቀምና ነገን የተሻለ ለማድረግ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

“ክህሎቶችን መገንባት፣ ሥራዎችን ማቀላጠፍ፣ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ የጀመረው ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ተከታታይ ቀናት ይቆያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review