በፌደራል መንግሥት ቁርጠኝነት ታሪካዊ ስኬት የሆኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሶማሌ ክልል እየተከናወኑ ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀዋል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
በዚሁ ወቅትም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ባደረጉት ንግግር፤ በመንግሥት ቁርጠኝነት የተመረቀው ብሎም የሚገነቡት ትላልቅ ፕሮጀክቶች የክልላችን ብሎም የሀገራችን ታሪካዊ ስኬቶች ናቸው ብለዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ፋይዳቸው ዘርፈ-ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ መሆኗን ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል እንደክልል ብሎም እንደሀገር በቁርጠኝነት እየተከናወኑ ያሉትን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥና ከድህነት የመላቀቅ ጉዞ ያፋጥናሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ በዚህም የሶማሌ ክልልን ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ሂደት እነዚህ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል በንግግራቸው።
ትናንት አጀንዳችን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ማስገባት ነበር፤ አሁን ደግሞ ትኩረታችን የምግብ ሉዓላዊነትንና ዘርፈ-ብዙ የልማት ተደራሽንትን ማረጋገጥ ነው ብለዋል። ይህን ከሀገር አልፎ ለአኅጉር የሚተርፍ ሐሳብ በማመንጨትና በመተግበር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እያበረከቱት ላለው ድንቅ ተግባር ምሥጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በዚሁ መሠረት ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የፌደራል መንግሥት ለሶማሌ ክልል ትኩረት መስጠቱንና በዚህም በተለያዩ ዘርፎች አስደናቂ ለውጦች መመዝገባቸውን አንስተዋል።