የከንቲባ አዳነች አቤቤ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት፡

You are currently viewing የከንቲባ አዳነች አቤቤ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት፡

እንኳን ለ2018 የኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔ በአል አደረሳችሁ!

ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለፈጣሪ አምላክ ምስጋና የሚቀርብበት፤ ከሰው ጋር ሰላም፣ ፍቅር እና አብሮነት የሚከናወንበት፤ አዲስ ተስፋና ብሩህ ዘመን የሚበሰርበት በዓል ነው።

በዩኔስኮ የተመዘገው የኦሮሞ ገዳ ሥርአት አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል የሀገራችንን መልከ-ብዝሃነት፤ ጥልቅ ዉበት ለመላዉ ዓለም ካሳዩ እና ካስተዋወቁ በዓላት መካከል አንዱ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድም እህት ህዝቦች ጋር በመሆን ባካሄደዉ መራር ትግል ከተቀዳጃቸው ድሎች መካከል አንዱ የኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔን ክብረ በዓል በጥንታዊ ስፍራው ማክበር መቻል ሲሆን ይህም ባለፉት 7 አመታት በከፍተኛ ድምቀት ባህላዊ እሴቱን እና ቱፊቱን ጠብቆ በመዲናችን አዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል።

የመዲናችን አጠቃላይ ህዝብም ከወንድም እህቱ የኦሮሞ ህዝብ ጋር በአብሮነት በሚያከብረው በዚህ ታላቅ በዓል ላይ እንደወትሮው ሌሎች የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ለበዓላቱ ድምቀት እና ባማረ መልኩ መጠናቀቅ እንደሚያደርገው ሁሉ አብሮነትን፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን በሚያጸና መልኩ፤ በከተማው ውስጥ ከሚኖሩ የኦሮሞ ሕዝቦችም ሆነ በእንግድነት ከሚመጡት ወገኖቹ ጋር በመሆን በዓሉ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ በመንገድ ጽዳት፣ በአደባባይ ማስዋብ እና በሌሎችም በርካታ በጎ ፈቃድ ስራዎች ከምንጊዜውም በላቀ መልኩ ለአገር ገጽታ ግንባታ፣ ለዘላቂ ቱሪዝም መስህብነት፣ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚያመች መልኩ በሕብረ ብሄራዊ አንድነት መንፈስ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።

መላው የከተማችን ነዋሪዎች በከተማችን የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ በዓላቱ ከዋዜማዉ አንስቶ እስኪጠናቀቁ ድረስ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በመሳተፍ እያበረከታችሁ ላለዉ እጅግ የላቀ ሚና እያመሰገንኩ፣ ይህ ተግባር ውብ እና ድንቅ ባህሎቻችን ከእኛ አልፈው ለመላዉ ዓለም የምናበረክታቸው፤ የእኛነታችን መለያ ጌጥ በመሆናቸው እንደወትሮው ሁሉ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል በድምቀት ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ባማረ መልኩ ለማክበር ያደረግነውን ቅድመ ዝግጅት ከዋዜማው ጀምሮ በጋራ በምናከናውነው ተግባር የከተማችንን የሰላም ተምሳሌትነት፣ የህዝባችንን የሰላም ዘብነት እና እንግዳ ተቀባይነት በማረጋገጥ ይሆናል።

በድጋሚ እንኳን ለ 2018 ኢሬቻ ሆረ-ፊንፊኔ ክብረ በዓል አደረሳችሁ!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review