የኢሬቻ በዓል

You are currently viewing የኢሬቻ በዓል

የሀገራችንን መልከ-ብዝሃነት እና ጥልቅ ውበት ለመላው ዓለም ካስተዋወቁ በዓላት መካከል አንዱ ነው

   የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

የኢሬቻ በዓል የሀገራችንን መልከ-ብዝሃነት እና ጥልቅ ውበት ለመላው ዓለም ካሳዩ እና ካስተዋወቁ በዓላት መካከል አንዱ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

ለ2018 የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ከንቲባ አዳነች እንዳሉት በዩኔስኮ የተመዘገበው የኦሮሞ ገዳ ሥርዓት አካል የሆነው የኢሬቻ በዓል የሀገራችንን መልከ ብዝሃነት እና ጥልቅ ውበት ለመላው ዓለም ካሳዩ እና ካስተዋወቁ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡

ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፤ ከሰው ጋር ሰላም፣ ፍቅር እና አብሮነት የሚከናወንበት፤ አዲስ ተስፋና ብሩህ ዘመን የሚበሰርበት በዓል መሆኑንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት  መልዕክት ገልፀዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድም እህት ህዝቦች ጋር በመሆን ባካሄደው መራር ትግል ከተቀዳጃቸው ድሎች መካከል አንዱ የኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔን ክብረ በዓል በጥንታዊ ስፍራው ማክበር መቻል መሆኑንም ገልፀው፣ ይህም ባለፉት 7 ዓመታት በከፍተኛ ድምቀት ባህላዊ እሴቱን እና ቱፊቱን ጠብቆ በመዲናችን አዲስ አበባ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዓሉን የመዲናዋ አጠቃላይ ህዝብም ከወንድም እህቱ የኦሮሞ ህዝብ ጋር በአብሮነት የሚያከብረው ታላቅ በዓል ስለመሆኑ ያወሱት ከንቲባዋ ሌሎች የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ለበዓላቱ ድምቀት እና ባማረ መልኩ መጠናቀቅ እንደሚያደርገው ሁሉ አብሮነትን፣ ወንድማማችነትን፣ እህትማማችነትን በሚያጸና መልኩ በከተማዋ ውስጥ ከሚኖሩ የኦሮሞ ሕዝቦችም ሆነ በእንግድነት ከሚመጡት ወገኖቹ ጋር በመሆን በዓሉ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ስለመደረጉ ገልፀዋል፡፡

እንደዚሁም በመንገድ ጽዳት፣ በአደባባይ ማስዋብ እና በሌሎችም በርካታ በጎ ፈቃድ ስራዎች ከምንጊዜውም በላቀ መልኩ ለሀገር ገጽታ ግንባታ፣ ለዘላቂ ቱሪዝም መስህብነት፣ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚያመች መልኩ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት መንፈስ ዝግጅት ስለመደረጉም አስረድተዋል።

በከተማዋ የአደባባይ በዓላት ሲከበሩ ለመላው የከተማዋ ነዋሪ በዓላቱ ከዋዜማው አንስቶ እስኪጠናቀቁ ድረስ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በመሳተፍ እያበረከተ ላለው እጅግ የላቀ ሚና ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ይህ ተግባር ውብ እና ድንቅ ባህሎቻችን ከእኛ አልፈው ለመላው ዓለም የምናበረክታቸው፣ የእኛነታችን መለያ ጌጥ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም እንደወትሮው ሁሉ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ ባማረ መልኩ ለማክበር የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት ከዋዜማው ጀምሮ በጋራ በሚከናወኑ ተግባራት የከተማዋን የሰላም ተምሳሌትነት፣ የህዝባችንን የሰላም ዘብነት እና እንግዳ ተቀባይነት በማረጋገጥ ይሆናል ብለዋል በማጠቃለያ መልዕክታቸው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review