አልባሳቱ የጋራ ማንነትና ትስስርን ለማጠናከር እንደሚያገለግል ተገልጿል
ኢሬቻ ምስጋና፣ ሰላምና መቻቻልን ዓብይ ትኩረቱ በማድረግ በአደባባይ የሚከበር በዓል ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአደባባይ ደምቀው ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ መሆን የቻለው ኢሬቻ ከማህበራዊ ፋይዳው ባለፈ የቱሪዝም መስህብ በመሆን እና ማንነትን በማስተዋወቅ ረገድም የራሱን ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
የኢሬቻ በዓል ትውፊታዊ ዳራን በተመለከተ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ያለ ፆታ፣ ዘር እና የእድሜ ልዩነት በዓሉን ለዘመናት በጋራ ሲያከብር ቆይቷል። የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የሚወጣው ታዳሚ እንደ ሳር እና አበባ ያለ እርጥብ ነገር በእጁ ይዞ ነው። የበዓሉ ታዳሚ የየአካባቢውን ባህል፣ አልባስና አጊያጊያጥ የሚያስተዋውቅበት መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል በዓሉ፡፡
በኢሬቻ በዓል ላይ በባህላዊ አልባሳት የተሽቀረቀሩ ወጣቶች ይበልጥ የዐይን ማረፊያዎች ሆነው መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ የመጡበትን አካባቢ የሚያንጸባርቁ አልባሳት የለበሱ፣ በቡድን ሆነው በተመሳሳይ የባህል አልባሳት ያሸበረቁ ወጣቶች፣ በአንገትና እጃቸውን እጅግ በተዋቡ ባህላዊ ጌጣጌጦች የተዋቡ ሴቶችም የኢሬቻ በዓል ልዩ ድምቀቶች ናቸው፡፡

ኢሬቻ ከኦሮሞ ሕዝብ ማንነት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ ታላቅ በዓል ነው የሚሉት ደግሞ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ዋና ጸሐፊ እና የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ናቸው፡፡ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት የሚለበሱ ባህላዊ አልባሳት የየአካባቢውን ማንነት በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። አልባሳቱ ከውበት በላይ የሆኑ ጥልቅ ትርጉሞችን ይይዛሉ ያሉት አባ ገዳ ጎበና፣ በተለይ የሕዝቡን ታሪክ፣ እሴቶች እና የማንነት እንደሚያንፀባርቁ ገልፀዋል።
በቋሚነት በኢሬቻ በዓል እንደሚታደሙ የተናገሩት አቶ ግርማ ቱፋ በበኩላቸው፣ ኢሬቻን የሚያደምቁት ባህላዊ አልባሳት ከኛ አልፈው የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ሳይቀር ይማርካቸዋል። እነዚህ አልባሳት የቱሪዝም ማዕከል ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን፣ የኦሮሞን ሕዝብ ባህል ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ብለዋል። ጎብኚዎች ስለ ልብሶቹ ታሪክና ትርጉም በመጠየቅ፣ የኦሮሞን ባህል የበለጠ ለመረዳትና ለማድነቅ ይነሳሳሉ ሲሉም አክለዋል።
በእርግጥም በኢሬቻ ወቅት የሚለበሱ አልባሳት እንዲሁ በዘፈቀደ የተመረጡ አይደሉም። እያንዳንዱ ልብስ፣ እያንዳንዱ ቀለም እና እያንዳንዱ ጥልፍ የራሱ የሆነ ታሪካዊ እና ባህላዊ ትርጉም አለው። ለምሳሌ ነጭ ልብሶች የንጽህና፣ የሰላም እና የአዲስ ጅማሬ ምልክት ናቸው። እነዚህ አልባሳት በኢሬቻ በዓል ወቅት በብዛት የሚለበሱ ሲሆን፣ የኦሮሞን ሕዝብ በጎ እና ሰላማዊ አኗኗርን የሚያንጸባርቁ ናቸው:: እንደዚሁም የጥልፍ ሥራዎች በኦሮሞ ባህል ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም አላቸው። የተለያዩ የእፅዋት እና የእንስሳት ቅርጾችን የሚያሳዩ ጥልፎች፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን ጥበብ ያንፀባርቃሉ።

በሌላም በኩል እነዚህ አልባሳት አንድ ወጣት ወንድ ወይም ሴት ወደ አዋቂነት ደረጃ ሲሸጋገር፣ በትዳር ሲጣመር ወይም ማህበራዊ ደረጃው ሲቀየር የሚለብሳቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃርም አልባሳቱ የተለያዩ ትርጉሞችን ሊይዙ ይችላሉ። የተለያዩ የጌጣጌጥ ዓይነቶች አልባሳቱን የበለጠ ማራኪ ከማድረግ ባለፈ የባለቤታቸውን ማህበራዊ ደረጃ፣ ሀብት እና የቤተሰብ ታሪክ ማሳያ ተደርገውም ይወሰዳሉ።
በኢሬቻ በዓል የሚለበሱ ባህላዊ አልባሳት እንደሌሎች ባህላዊ ቅርሶች ሁሉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ናቸው። አባቶች እና እናቶች ልጆቻቸውን በበዓሉ ወቅት ምን አይነት ልብስ መልበስ እንዳለባቸው ሲያስተምሩ፣ የልብሶቹን ትርጉም እና አስፈላጊነት አብረው ያስተላልፋሉ። ይህ ሂደት ባህሉ ዘመናትን ተሻግሮ እንዲቀጥል ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል።
የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ወቅት የሚታየው የአልባሳት ትዕይንት ዘመናዊው ትውልድም ይህንን በዓል እየተቀበለና እየተንከባከበ መሆኑ አንድ ማሳያ ስለመሆኑም አባ ገዳ ጎበና ሆላ ይገልጻሉ። ብዙ ወጣቶች በበዓሉ ላይ ለመታደም ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ፣ በባህሉ የመኩራራት ስሜት ይሰማቸዋል ሲሉም አክለዋል አባ ገዳ ጎበና፡፡ በእርግጥም አባ ገዳው እንደሚሉት የኢሬቻን ማንነት በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች የዘመናዊ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት እንዲተዋወቅ ትልቅ መድረክ ፈጥሯል። የልብሶቹ ውበት በፎቶና ቪዲዮ አማካኝነት በስፋት እየተሰራጨ ነው።
ምንም እንኳን የኢሬቻ አልባሳት ባህሉን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ቢጫወቱም፣ አንዳንድ ፈተናዎችም ያጋጥሟቸዋል። ለምሳሌ የዘመናዊነት ተፅዕኖ በባህላዊው የአልባሳት ምርት ላይ ሊመጣ ይችላል የሚለው አንዱ ስጋት ነው። አንዳንድ ሰዎች ባህላዊ ጥልፎችን እና ዲዛይኖችን ከዘመናዊ ቁሶች ጋር በማቀላቀል የመነሻውን ትርጉም ሊለውጡ ይችላሉና ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉ አባ ገዳ ጎበና ሆላ መክረዋል። አክለውም፣ እነዚህ እርስ በእርስ ለመተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚፈጥሩት አለባበሶች ስርዓቱን የተከተሉ መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ከውበት በላይ የሆኑት እነዚህ አልባሳት፣ ባህሉን በማስተዋወቅ፣ ትውልዶችን በማገናኘት እና የቱሪዝም ፍሰትን በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል የሚሉት ደግሞ የባህልና ሰላም ተመራማሪ ወሰን ባዩ (ዶ/ር) ናቸው። እነዚህን አልባሳት መንከባከብ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ የኦሮሞን ባህል ከትውልድ ትውልድ ለማሸጋገር አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የበዓሉ አከባበር በብዙ ረገድ እጅግ አስደሳች እንደሆነ ገልፀው፣ በተለይ ልዩ ልዩ አልባሳቱ የማህበረሰቡ የእርስ በእርስ መስተጋብር ከማጎልበቱም በላይ ለቱሪዝም ዕድገት ሚናው የጎላ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባለፈም እንደ ኢሬቻ ያሉ የመሳሰሉ የአደባባይ በዓላት ለሀገር ግንባታ ሂደት እጅግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል የባህልና ሰላም ተመራማሪ ወሰን (ዶ/ር)፡፡
የባህልና ሰላም ተመራማሪ ወሰን (ዶ/ር) ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሊሰራባቸው ይገባል ካሏቸው ጉዳዮች መካከል የባህላዊ አልባሳት አምራቾችን እና ዲዛይነሮችን ማበረታታት እና ድጋፍ ማድረግ የሚለው ተጠቃሽ ነው። በተመጣጣኝ ዋጋ የባህላዊ አልባሳትን የሚያመርቱ ማህበራትን ማቋቋም። ወጣቶችን ስለ አልባሳቱ ታሪክ እና ትርጉም ለማስተማር ባህላዊ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ማዘጋጀት ይገባል ይላሉ።
ቀይ፣ ጥቁርና ነጭ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በአንድ ላይ በህብር ሆነው ሲመጡ በፍጥነት ለኢትዮጵያዊ ተመልካች የኦሮሞ ባህል አልባሳት ቀለማትን ምስል ይከስታሉ። በኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው የኦዳ ዛፍ ምልክት ነው። ይህ የኦዳ ዛፍ ምልክት በቀሚሶች፣ ሱሪዎችና ኮቶች ላይ በሕትመት ጥበብ ገብቶ ተጨማሪ ፈርጥ በመሆን ሲያገለግልም ይስተዋላል። በአዲስ ዓመት መባቻ በመስቀል እና በተለይም ኢሬቻ በዓል የባህል አልባሳቱ በብርቱ ተፈላጊ እየሆኑ የመጡትም ለዚሁ ነው፡፡

እንደ የባህልና ሰላም ተመራማሪ ወሰን (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ኢሬቻም ሆነ ሌሎች የአደባባይ በዓላት በባህርያቸው ዜጎችን በአንድ መድረክ የሚያሰባስቡ በዓላት ናቸው፡፡ ዜጎች በዓሉን ለማክበር በአንድ መድረክ ላይ ሲገናኙ ይበልጥ መገነዛዘብ ይጀምራሉ፡፡ የባህል ልውውጥ ከማድረጋቸውም በላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ ባህሎች ያሸበረቀች ውብ ሀገር መሆኗን ይረዳሉ፡፡
የባህልና ሰላም ተመራማሪ ወሰን (ዶ/ር) እንደመስቀልና ኢሬቻ ያሉ በዓደባባይ የሚከበሩ በዓላትን አንድምታ አስመልክተው ባጋሩን ሙያዊ ማብራሪያ የኢትዮጵያውያን የእርስ በእርስ መስተጋብር በስፋት የሚንጸባረቅባቸው በዓላት ናቸው ብለዋል፡፡
ኢሬቻን አድማቂዎቹ የባህል አልባሳት በዚህ ደረጃ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ከመጣ ኢኮኖሚያዊ አበርክቷቸውም ቀላል አይደለም:: የሀገር ባህል አልባሳት ከማስተዋወቅ ባለፈ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በኢሬቻ እና በሌሎች በዓላት የሀገር ባህል ልብሶችን የመልበስ ልማድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡

ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከክረምት ወደ ጸዳል ላሻገረ አምላክ ምስጋና የሚሰጥበት የኢሬቻ በዓል ክረምቱን ከበረዶ፣ ከጎርፍና ከውርጭ በሰላም አልፈው ወደ ብርሃን ሽግግር የሚደረግበት ጊዜ በመሆኑ በተለይ የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪውን አንድ ላይ ሰብሰብ በማለት ያመስግናል። በዓሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ በዓል ባህላዊ አልባሳትን በመልበስ የጋራ ማንነትን እና ትስስርን ለማጠናከር እንደ መድረክ ያገለግላል።
በሳህሉ ብርሃኑ